ኢሳት (ታህሳስ 21 ፥ 2009)
የታዋቂው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የቀብር ስነስርዓት የፊታችን ዕሁድ በአዲስ አበባ ከተማ ቅድስ ስላሴ-ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ታወቀ።
የጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር አስከሬን አዲስ አበባ ሲደርስ የመቀበልና የቀብር ስነስርዓቱን የሚያስተባብር በአትሌቶች የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙ ታውቋል።
ምሩፅ ካረፈበት ጊዜ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ህዝብ እየተሰጠ ያለው ምላሽ እንዳስደሰታቸውም ልጆቹ ሄኖክ፣ ካህሳይና፣ ሚካኤል ምሩጽ ገልጸዋል።
ማክሰኞ ታህሳስ 18: 2009 በካናዳ ቶሮንቶ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን ጸሎተ ፍትሃት በተደረገ የሻምበል ምሩጽ ይፍጠር አስከሬን ዕሁድ ጠዋት አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን፣ በዕለቱ ከቀትር በኋላም የቀብር ስነስርዓቱ ይፈጸማል። የጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ህልፈት ተከትሎ በኢትዮጵያ በተሰጠው ምላሽ፣ የተደሰቱትና በቶሮንቶ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን የአሸኛኘት ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሻምበል ምሩፅ ልጆች ሄኖክ፣ ካህሳይና ሚካዔል ምሩፅ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ለህዝብ ምስጋና አቅርበዋል፥ ለአባታቸውም መስክረዋል።
ከ35 አመታት በፊት እኤአ በ1980 በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺህና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች የድርብ ወርቅ ባለቤት የነበረው የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር፣ ከዚያ 8 አመታት ቀደም ብሎ እኤአ በ 1972 በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺህ ሜርት የነሃስ ሜዳሊያ መግኘቱም ይታወሳል። በሁለት የኦሎምፒክ የሶስት ሜዳሊያዎች ባለቤት የነበረውና በመካከለኛ ርቀት ሩጫ በአለም ላይ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ72 ዓመቱ ባለፈው ሃሙስ ታህሳስ 20, 2009 በካናዳ ቶሮንቶ ማረፉ ይታወሳል።
የብሪታኒያ ድረገፅ ኢትዮጵያዊው ምሩፅ ይፍጠር ዝነኛው ሯጭ አረፈ በማለት የአሜሪካው ቦስተን ግሎብ ሲዘግብ፣ ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር ከዚህ አለም በሞት ተለየ በማለት ዜናውን ያሰራጨው ደግሞ አትሌቲክስ ዊክሊ ነበር። ታላቁ የኦሎምፒክ ሰው ምሩፅ ይፍጠር አረፉ በማለት ስካይ ስፖርት ከብሪታኒያ ሲዘግብ፣ የጃፓኑ ጃፓን ታይምስ ዝነኛው ኢትዮጵያዊ ሯጭ አለፈ ሲል ለንባብ አብቅቷል።
የታዋቂው ኢትዮጵያዊ ሯጭ ምሩፅ ይፍጠርን ህልፈት ተከትሎ አለም አቀፍ ሚዲያዎች የስፖርት ተቋማት፣ ጀግናውን አትሌት የሚያስታውሱ ዘገባዎች አቅርበዋል። አለም አቀፉ የአተሌቲክስ ፌዴሬሽን ከሞንቴ ካርሎ ሞናኮ እጅግ ዝነኛው ሯጭ ምሩጽ ይፍጠር አለፈ በማለት ሲገልጽ፣ ዝነኛው ምሩጽ ይፍጠር በካናዳ ቶሮንቶ አክብሮት ተደረገለት በማለት ጸሎተ ፍትሃቱን ያስታወሰው ደግሞ የካናዳው ሲቢሲ ነው። ዝነኛው ሯጭ ምሩፅ ይፍጠር የኢትዮጵያ ስጦታ በማለት የገለጸው ኦል አፍሪካን የተባለው ድረገጽ ሲሆን፣ የድርብ ኦሎምፒክ ባለቤት የገለጸው ደግሞ ኢንሳይድ ጌምስ የተባለው ነው።
ትልልቆቹ የአሜሪካ የዜና አውታሮች አሶሼትድ ፕሬስ፣ the New York Times, Los Angeles Times, ESPN, Euro Sport, እንዲሁም the Economic Times, Belfast Telegraph, የጀግናው አትሌት ዜና ህልፈት ከዘገቡት ውስጥ በቀዳሚነት የጠቀሳሉ።