ምዕራባውያን አዲስ አመትን ለመቀበል የጸጥታ ቁጥጥር ማጠናከራቸው ተገለጸ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፥ 2009)

የፊታችን ዕሁድ የሚከበረውን 2017 የፈረንጆች አዲስ አመት ለመቀበል አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን ሃገራት የጸጥታ ቁጥጥር ማጠናከራቸው ተገለጸ።

በዚህ በአሜሪካ ቅዳሜ ምሽት በኒው ዮርክ ከተማ የሚከበረውን የዋዜማ ስነስርዓት በማስመልከት የከተማዋ ፖሊስ 7 ሺ የፖሊስ አባላትን በማሰማራት የጸጥታ ቁጥጥር ማድረግ መጀመሩን የአሜሪካን ፖሊስ አርብ አስታውቋል።

በቅርቡ በጀርመን በርሊን ከተማ የተፈጸመው የሽብር ድርጊት ለጸጥታ ቁጥጥሩ ምክንያት የሆነ ሲሆን፣ የበአሉ ዝግጅት ወደሚከናወንበት አደባባይ (ታይም ስኩዌር) የሚወስዱ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ተደርገዋል።

በኒው ዮርክ ከተማ በሚካሄደ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠብቅና በተለያዩ ጊዜያትና ሃገራት የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶች ግምት ውስጥ በማስገባት ለጸጥታ ቁጥጥሩ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የከተማዋ ፖሊስ ሃላፊ ካርሎስ ጎሜዝ ገልጸዋል።

በፈረንሳይና በቅርቡ በጀርመን በተሽከርካሪዎች የተፈጸመ አይነት የሽብር ድርጊት እንዳይከሰት ለመከላከል በአሸዋ የተሞሉ ከ60 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዋና ዋና መንገዶች ዘግተው እንደሚቆሙ ፖሊስ አስታውቀዋል።

አሜሪካ የአዲስ አመት አከባበሩን በማስመልከት የጸጥታ ቁጥጥሯን ብታጠናክርም ይደርሳል ተብሎ የተሰጋ የሽብር ጥቃት ስጋት እንደሌለ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ጀምስ ኦ-ኔይል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የኒውዮርክ ከተማ የአዲስ አመት ዋዜማን ለማክበር ለጸጥታ ቁጥጥር የሰጠችው ግምትና ወጪ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ለበአሉ አከባበር ወደ ዋናው አደባባይ የሚገቡ እንግዶች በርካታ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ማለፍ የግድ የሚላቸው ሲሆን፣ ሄሊኮፕተሮችን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የተባሉ የደህንነት ቁሳቁሶች አገልሎት ላይ እንደሚውሉ የኒው ዮርክ ከተማ ባለስልጣናት ይፋ አድርጓል።

አውስትራሊያን ጨምሮ የአዲስ አመቱን በልዩ ዝግጅት የሚቀበሉ በርካታ የአለማችን ሃገራት ተመሳሳይ የጸጥታ ቁጥጥር ተግባራዊ ማድረጋቸው ታውቋል።

የጀርመን፣ የብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይና፣ ሌሎች ሃገራት ህዝብ በሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች የጸጥታ አባላትን በማሰማራት የ24 ሰዓት ቁጥጥር እያደረጉ ሲሆን፣ ይኸው ልዩ ጥንቃቄ ከሩሲያዋ ሞስኮ እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን ድረስ መዝለቁም ተነግሯል።