ታኀሳስ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአሁን በፊት የባህርዳር ነዋሪዎች ባህርዳር ላይ የሚገኘው የአባይ ድልድይ ችግር አጋጥሞታል በማለት በልዩ ልዩ ስብሰባዎች ቢያሳስቡም የገዢው መንግስት አመራሮች በቅርቡ ተለዋጭ ይሰራል በማለት ሲሸነግሉ ቆይተዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የድልድዩ ወደ ሰሜን መውጫ ክፍል ላይ ያለው ንጣፍ ዝቅ እያለ በመሄዱ ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ በቦታው የፌደራልና የክልሉ ፖሊሶች ተመድበው፣ መኪኖች በድልድዩ ግማሽ መስመር በጥንቃቄ እንዲተላለፉ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ድልድዩ ወደ ውስጥ በመስመጡ የትራፊክ መጨናነቅን ፈጥሯል፡፡ከጎንደርና ከሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል የሚመጡትም ሆነ ወደ ሰሜኑ ክፍል የሚጓዙ መኪኖችና ታክሲዎች ረጃጅም ሰልፍ ይዘው እንደሚታዩ ዘጋቢያችን ገልጿል። ኢሳት የችግሩን አሳሳቢነት ከወራት በፊት ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።