(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14/2010)
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽም መመሪያ መውጣቱን የመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ።
የአውሮፓ ህብረት፣ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ፣የብሪታኒያና የጀርመን መንግስታት የተቃወሙትን ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ የወጣው ዝርዝር መመሪያ የአደባባይ ሰልፍና የአዳራሽ ስብሰባን ጭምር ከልክሏል።
ማናቸውም ወገን ባለስልጣናት ጭምር በጸጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ ለመስጠት ኮማንድ ፖስቱን ማስፈቀድ እንዳለባቸውም አሳስቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው መመሪያ ላይ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማወክ፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣የሕግ አስከባሪዎችን ተግባር ማወክ፣በትምህርት ተቋማትና በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች አድማ ማድረግ፣ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ተግባራትን መፈጸም የሚሉትና ሌሎችም ተዘርዝረዋል።የአውሮፓ ህብረት፣አሜሪካ፣ብሪታኒያና ጀርመን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተቃውመውታል።
ነገር ግን ሀገራቱ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም የሕወሃት ስርአት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስፈጸሚያ ዝርዝር መመሪያ በማውጣት የአደባባይ ሰልፍና የአዳራሽ ስብሰባን ጭምር መከልከሉን አስታውቋል።
የፖለቲካ አጀንዳ ማስተጋባትን ሲከለክል ስብሰባ ለማድረግ ፍቃድ መጠየቅን ደግሞ እንደ ግዴታ አስቀምጧል።
የሰአት እላፊ አዋጅ በሚታወጅባቸው አካባቢዎች ከሰአት እላፊ በኋላ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ግለሰቦች ላይ የጸጥታ ሃይሎች ርምጃ እንዲወስዱ ማለትም መግደልን ጨምሮ ስልጣን ሰጥቷል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፈጻጸም መመሪያ ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ በጸጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት የተከለከለ መሆኑንም ያሳስባል።
ይህም ክልሎችና የክልል ባለስልጣናት በአካባቢያቸው በተፈጸሙ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ጭምር መግለጫ እንዳይሰጡ የሚከለክል ነው።
መስጠት ከፈለጉም ኮማንድ ፖስቱ ሲፈቅድላቸው ብቻ የሚፈጸም ይሆናል ይላል መመሪያው።
ይህም የክልሎችን ሕጋዊ መብትና ስልጣን የገደበ መሆኑም ተመልክቷል።
በአፈጻጸም መመሪያው የፖለቲካ አጀንዳዎችን ማስተጋባት የተከለከለ መሆኑንም ይገልጻል።
የፖለቲካ አጀንዳን ማስተጋባት ማለት ምን ማለት ነው? የሚለው በግልጽ አልተቀመጠም።ይህ ማለት በማናቸውም ስፍራና ሁኔታ ሃሳብን የመግለጽ መብት በግልጽ ተገድቧል ማለት ነው ወይ የሚሉ ጥያቄዎች ቢሰነዘሩም ምላሽ ግን የሚሰጣቸው አልተገኘም።
አከራዮች የተከራይን ማንነት በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ያስገድዳል።