በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቁ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 14/2010)

በኢትዮጵያ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተመለከተ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ያሰሙትን ተቃውሞ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ማይክ ሬነር ከትላንት በስቲያ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተጠርተው ማብራሪያ መጠየቃቸውን የውስጥ ምንጮችን በመጥቀስ የወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁን ተከትሎ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይነር ወዲያውኑ ባወጡት መግለጫ የአዋጁን መውጣት ተቃውመዋል።

መብትን በመገደብ መፍትሄ አይገኝም ያሉት ማይክ ሬነር ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዳይገልጹ የሚደረግ ገደብ የሕዝብን ድምጽ አለመስማት ነው በማለት አዋጁ ተግባራዊ እንዳይሆን ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይሁንታ የሚወጣው የአሜሪካው አምባሳደር መግለጫ ያስቆጣው የኢትዮጵያ መንግስት አምባሳደር ማይክ ሬነርን ሰኞ ዕለት ጠርቶ ማነጋገሩም ተመልክቷል።

ሪፖርተር እንደዘገበው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሃላፊዎች የአምባሳደሩ መግለጫ ጠቃሚ እንዳልሆነና ለሰላም ሒደቱ እንደማያግዝ ነግረዋቸዋል።

አምባሳደሩም መግለጫውን በአሉታዊነት እንዳይመለከቱት ጠይቀዋል።

የካቲት 9/2010 ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም በሚል የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰሙ የምዕራቡ አለም መንግስታት ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በተጨማሪ ብሪታኒያና ጀርመን ይጠቀሳሉ።

የአውሮፓ ሕብረትም በተመሳሳይ አዋጁ እንደሚያሳስበው በመግለጽ በአጭርግዜ  እንዲነሳም ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።