(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 9/2009) በኢትዮጵያ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ ከተከሰተው ድርቅ ጋር በተያያዘ የአርብቶ አደሮች ከብቶች በከፍተኛ ደረጃ እያለቁ መሆናቸውን የአለም የምግብ ድርጅት ፋኦ አስታወቀ።
እስካሁን ብቻ 2 ሚሊየን ከብቶች ሞተዋል።
ከብቶቹ በከፍተኛ መጠን እያለቁ የሚገኙት በግጦሽ ሳርና በውሃ እጦት መሆኑን ድርጅቱ ገልጿል።
በኢትዮጵያ ከድርቅ ጋር በተያያዘ የተረጂዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ከምግብ እጥረት ጋር በተገናኘ ሰዎችም ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ከ12 ሰዎች አንዱ በአካባቢው በረሃብ የተጎዳ መሆኑ ይገለጻል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ብቻ የተረጂዎች ቁጥር 3 ነጥብ 3 ሚሊየን መድረሱን የአለም የምግብ ድርጅት ፋኦ አስታውቋል።
በተለይም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከብቶች እያለቁ መሆናቸው ለአርብቶ አደር ሰዎች የሕይወትና የሞት ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት የዜና ማእከል ዘግቧል።
እናም በተጠቀሱት አካባቢዎች 2 ሚሊየን የሚደርሱ ከብቶች እስካሁን መሞታቸውን ዘገባው አመልክቷል።
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ እጅግ እየከፋ የመጣው ድርቅ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ እያጋለጠ ነው ሲል ኦክስፋም አስጠንቅቋል።
ኦክስፋም በመግለጫው እንዳሰፈረው ቀድሞ ከነበረው በተጨማሪ 700ሺ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ረሃብ ተጋልጠዋል።
በአጠቃላይ አስቸኳይ የእለት ምግብ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 8 ነጥብ 5 ሚሊየን መድረሱንም አረጋግጧል።
የተባበሩት መንግስታት ያወጣውን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ኦክስፋም እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ እንደ ኣውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 እንደነበረው ረሃብ እስከ 260 ሺ ሰዎችን ሊገድል ይችላል።