ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2009)
በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የሚገኝ ወህኒ ቤት በአርበኞች ግንቦት 7 ታጣቂዎች መሰበሩንና ከ60 በላይ እስረኞች መለቀቃቸው ተገለጸ። ወህኒ ቤቱን ለመስበር የተካሄደው ይኸው ጥቃት ሰዓታት እንደወሰደ የንቅናቄው የመስክ አመራሮች የገለጹ ሲሆን፣ አንድ የጥበቃ አባል ሲገደል፣ ሶስቱ መቁሰላቸው ተመልክቷል።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ታጣቂዎች በሰሜን ጎንደር ዞን በወገራ ወረዳ ችንፉዝ ሲላሪ ከተማ በሚገኝ ልዩ እስር ቤት ሰኞ ምሽት በፈጸሙት ጥቃት ከ60 በላይ እስረኞች መለቀቃቸውን የንቅናቄው የሰሜን ጎንደር ዕዝ አመራሮች ለኢሳት ገለጹ።
በከተማዋ ለአምስት ሰዓታት ያህል በተካሄደው በዚሁ እስረኞችን የማስለቀቅ ዘመቻ አንድ የእስር ቤቱ ጥበቃ መሞቱንና ሌሎች ሶስት ደግሞ መቁሰላቸውን አመራሮቹ ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።
ከንቅናቄው በኩል መጠነኛ ጉዳት መድረሱን ያረጋገጡት የንቅናቄው ተወካዮች በስቃይ ላይ የነበሩ እስረኞችን ለማስለቀቅ ነበር ያሉት ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አክለው ገልጸዋል።
በዚሁ ዘመቻ ከእስር ቤቱ ያመለጡና በንቅናቄው እጅ ስር እንደሚገኙ ለኢሳት የተናገሩት እስረኛ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ነዎት በመባል ለእስር መዳረጋቸውን አስረድተዋል።
ከእርሳቸው ጋር በርካታ እስረኞች ማምለጥ መቻላቸውን የገለጹት እኚሁ ታሳሪ ከእስር ቤቱ ያመለጡ እስረኞች ግማሾቹ ወደ ንቅናቄው መቀላቀላቸውንና ሌሎችም ወደተለያዩ ቦታዎች መሄዳቸውን አክለው አስረድተዋል።
እስር ቤቱን በመጠበቅ ላይ የነበሩ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ለተወሰነ ጊዜ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ቦታውን ለቀው እንደሸሹ ከእስር ቤቱ ለማምለጥ የቻሉ እስረኞች አክለው ተናግረዋል።
በንቅናቄውና በመንግስት የጸጥታ አባላት መካከል ተካሄዶ በነበረው የተኩስ ልውውጥ አንድ የንቅናቄው አባል የመቁሰል አደጋ እንደደረሰበትና በዘመቻው ተካፍለው የነበሩት አባላት ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ የሰሜን ጎንደር ዕዝ ገልጿል።
የመንግስት ባለስልጣናት ከወራት በፊት በሰሜን ጎንደር አካባቢ ጥቃት ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ የንቅናቄው ታጣቂዎች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
ሰኞ ምሽት በወገራ ወረዳ ችንፉዝ ሲላሪ ከተማ የደረሰን ጥቃት በተመለከተ ከመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።