(ኢሳት ዲሲ– ጥር 24/2018)የትግራይ ምሁራን የሕወሃትን አገዛዝ በማውገዝ ከሕዝብ ጋር እንዲቆሙ የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን/ ጥሪ አቀረቡ።
ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት የትግራይ ምሁራን ሀገርን እየከፋፈለና የግጭት መንስኤ የሆነውን ህወሃት ባለመውገዝ ዝምታን መምረጣቸው አግባብ አይደልም።
ሕወሃትን የትግራይ ሕዝብ አንድ ባለመሆናቸውም በዘር ላይ የተመሰረተ ጥቃት እንዳይኖር ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም ሁለቱ ድርጅቶች አሳስበዋል።
የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ እና የአርበኞች ግንቦት ሰባት የጋራ መግለጫ እንደሚለው ሕወሃት ሕዝብን በቋንቋና በብሔር እየከፋፈለ ሀገሪቱን ለእርስ በርስ ግጭት እየዳረገ ነው።
ይህንን የሚያደርገው የጋራ እሴቶችን በመሸርሸርና የሕዝቡን የአንድነት ታሪክ ጥላሸት በመቀባት ነው ብለዋል።
ሕወሃት በትግራይ ሕዝብ ስም እራሱን ወክሎ በርካታ በደል እየፈጸመ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።
“ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው” በሚል ስብከት የሚሰራቸውን ወንጀሎች በሕብረተሰቡ ስም በመፈጸሙ ሕዝቡ በጥርጣሬ እንዲተያይ አድርጎታል ነው ያለው።
እንደ መግለጫው የትግራይ ተወላጆች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ለረጅም ዘመናት በአብሮነትና በአንድነት የኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ይሁንና በተለያዩ ሁኔታዎች በማባበልና አባል እንዲሆኑ በማስቻል ሕወሃት በሕዝብ ላይ ለሚፈጽማቸው ጥቃቶች መረጃ አቀባይ፣ጉዳይ ፈጻሚና የአገዛዙ የድጋፍ ሃይል በማድረግ ሲጠቀምባቸው ኖሯል።
በዚህም ምክንያት የሕወሃት ካድሬዎች የበቀል ርምጃ ሲወሰድባቸው በሌላ በኩል ከአገዛዙ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያልነበራቸው የትግራይ ተወላጆች የጥቃት ሰለባ መሆናቸው አግባብ አይደለም ብሏል መግለጫው።
እናም የዚህ አይነቱን በዘር ላይ የተመሰረተ ጥቃት መከላከል የሚያስፈልገው ኢፍትሃዊ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ ሰላማችንና አንድነታችን አደጋ ስላለው ነው ሲል የሁለቱ ድርጅቶች መግለጫ አመልክቷል።
ይህም ችግር የተፈጠረው አገዛዙ “ሕወሃትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው” በማለቱ መሆኑንም በምክንያትነት አስቀምጧል።
ሕወሃት ላለፉት 25 አመታት በሕዝብ ላይ ጉዳት ሲያደርስ የትግራይ ምሁራን ዝምታን መምረጣቸው አግባብ እንዳልሆነም መግለጫው አሳስቧል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባትና የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን/ በመግለጫው የትግራይ ምሁራን ዝምታቸውን ትተው ከሕዝቡ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የሕወሃት አገዛዝ በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጭፍጨፋ በማውገዝ በቅርቡ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።