ሕወሃት ገለልተኛ መርማሪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ እንዲፈቅድ ቀነ ገደብ ተሰጠው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 25/2010)

የኢትዮጵያው አገዛዝ በሀገሪቱ የተፈጸመውን ግድያና እስር እንዲሁም የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚያጣሩ ገለልተኛ መርማሪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ እንዲፈቅድ ቀነ ገደብ ተሰጠው።

በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገለልተኛ አጣሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ካልፈቀደ ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ የሕግ ውሳኔ ለኮንግረሱ እንደሚቀርብ የአሜሪካ መንግስት አስጠንቅቋል።

ይህ ማስጠንቀቂያ ለኢትዮጵያው አገዛዝ እንደተገለጸለት ለማወቅ ተችሏል።

ኤች አር 128 በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲመሰረት የሚያስገድድ በአሜሪካ መንግስት የተዘጋጀ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ነው።

በኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝ አርቃቂነት የተዘጋጀው ይህ የውሳኔ ሃሳብ በኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍማን ከፍተኛ ግፊት ከ60 በላይ የሕዝብ ተወካዮች እንዲደግፉት ተደርጓል።

በአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነትን ያገኘው ኤች አር 128 ለኮንግረሱ ለመቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ሆኖም የኢትዮጵያው አገዛዝ ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ በጸረ ሽብር ዘመቻው አንተባበርም በማለቱ በአሜሪካ የመከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ለጊዜው እንዲዘገይ ተደርጎ ነበር።

ይህንኑ ተከትሎ ኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍማን፣ በኮንግረስ ማን ክሪስ ስሚዝና የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውንስል ባደረጉት ግፊት የውሳኔ ሀሳቡ እንደገና እንዲታይ ለማድረግ ጉዳዩ ዳር እየደረሰ ይገኛል።

ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ሲቪክ ተቋማትን አስተባብረው በተያዘው ሳምንት በአሜሪካ ምክር ቤት የአብላጫ ድምጽ ያለው የሪፐብሊካን ፓርቲ መሪን ኬቨን ማካርቲን በጉዳዩ ላይ በካፒቶል ሒል ተገኝተው አንጋግረው ነበር።

ሚስተር ኬቨን ማካርቲ ታዲያ በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ገለልተኛ አጣሪዎች እንዲገቡ ካልፈቀደ ረቂቅ የውሳኔ ሕጉ በቅርቡ ለኮንግረሱ ይቀርባል ባሉት መሰረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 28/2018 ድረስ በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ ምላሽ ካልሰጠ ወደ ተግባር ርምጃ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ማካርቲ ይህንኑ አስመልክቶ በላኩት ደብዳቤ እስከተጠቀሰው ቀን የኢትዮጵያው አገዛዝ የተባበሩት መንግስታት ገለልተኛ አጣሪዎች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ ካልተፈቀደ ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ የውሳኔ ሕግ በኮንግረሱ እንዲጸድቅ ለውይይት ይቀርባል ።

ይህንኑ የቀነ ገደብ መልዕክትም ለኢትዮጵያው አገዛዝ እንደተገለጸለት ኬቨን ማካርቲ ገልጸዋል።