የአርበኞች ማህበር ገንዘብ በአመራሮቹ እየተመዘበረ እንደሆነ ታወቀ

ግንቦት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አንድነት ማህበር ሊቀመንበርና አጋሮቻቸው የማህበሩን ሃብትና ንብረት ያለአግባብ ለግል ጥቅማቸው እያዋሉትና እየመዘበሩት እንደሚገኙ፣ አንዳንድ የማህበሩ አባላት ለዝግጅት ክፍላችን ገለፁ።

ቅዱስ ሃብት በላቸው ከአውስትራሊያ ባጠናቀረው ዜና መሰረት የማህበሩ ሊቀመንበር የሆኑት ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ከጥቂት ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ቁጥሩ ቀላል የማይባል ጥሬ ገንዘብና ንብረት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል። ከዚህም መካከል በዓመት 800 ሺህ ብር ከሚከራየው ህንፃ 240 ሺህ ብር፣ እንዲሁም ካሳንቺስ አካባቢ የሚገኘው የማህበሩ ንብረት ከሆነው ቡና ቤት ኪራይ የሚገኘው 150 ሺህ ብር የት እንደሚገባ ተለይቶ እንደማይታወቅ የማሕበሩን ም/ፕሬዚዳንት ጨምሮ ሌሎች የማህበሩ አባላት አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የአዲስ አበባ መስተዳድር ለአቅመ ደካማ የማህበሩ አባላት እንዲከፋፈል የሰጠው 15 የቀበሌና 30 የኮንዶምኒየም ቤቶች ውስጥም የማህበሩ ፕሬዚዳንትና ጥቂት አመራሮች የግል ቤት እያላቸው ለራሳቸው ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ፤ የተቀረውንም ቢሆን አብዛኛውን ለቤተሰቦቻቸውና እነርሱ ለሚቀርቧቸው ጥቂት አባላት ማከፋፈላቸው ታውቋል። የወያኔ መንግስት ለይምሰል የሚጥልላቸው ዳረጎትም ሆነ፤ ከበጎ አድራጊዎች ለማህበሩ የሚለገሰው ገንዘብና ንብረት የጥቂት ሰዎች ኪስ እንደሚገባ የሚናገሩት እነዚሁ ቅሬታ ያላቸው የማህበሩ አባላት፣ በዚህ የኑሮ ውድነት ጣራ በነካበት ወቅት ለአርበኞቹ የሚከፈላቸው ገንዘብ በወር ከ150 ብር ያልበለጠ ገንዘብ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል አቤቱታ ቢያቀርቡም ሰሚ ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ችግር እየተሰቃዩ መሆናቸውን አክለው ገልፀዋል። በዚህም የተነሳ አቅሙ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከጎናቸው በመቆም ድጋፍ ያደርግላቸው ዘንድ ተማጽነዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማህበር ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ድረስ በዱር በገደሉ ተማርተው የፋሺሽት ኢጣሊያን ጦር ድል አድርገው ከአገር ባባረሩ አርበኞች የተቋቋመ አንጋፋ ማህበር ነው።የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሀን አስታጥቄ አባተ፣ የቀረቡት አቤቱታዎች አግባብነት የሌላቸው ለመሆናቸው ማስረጃ አለኝ በማለት ለሪፖርተር ተናገረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide