ኢሳት (ሰኔ 28 ፥ 2008)
የአረና ፓርቲ አባል በሳምንቱ መጨረሻ ባልታወቁ ሰዎች መገደሉ ተገለጸ። የአረና ፓርቲ በማህበራዊ መድረኩ እንዳስታወቀው ወጣት ዝናቡ ሃይሉ ባልታወቁ ሰዎች የተገደው በሳምንቱ መጨረሻ ሲሆን፣ ኩርመዓጋ በተባለ የአፋር ክልል ውስጥ ሞቶ መገኘቱም ተመልክቷል።
በቅፅል ስሙ ሴንቸሪ በሚል የተጠቀሰው ዝናቡ ሃይሉ አርብ ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓም ከጓደኞቹ ጋር ምሳ ከበላ ከሰዓታት በኋላ ሞቶ መገኘቱን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።
ከግድያው ጋር በተያያዘ 5 ግለሰቦች በጥርጣሬ የታሰሩ ሲሆን፣ አስከሬኑም በመቀሌ አይደር ሆስፒታል ምርመራ እንደተደረገለት መረዳት ተችሏል።
ዕድሜው 35 እንደሆነ የተገለጸው ዝናቡ ሃይሉ፣ በምርጫ 2007 አረናን ለማጠናከር ህንጣሎ ዋጀራት በተባለ አካባቢ መንቀሳቀሱን ያስታወሰው ዘገባ፣ በዚህም በተደጋጋሚ መታሰሩን እንዲሁም የድብደባ ወንጀል እንደተፈጸመበት ዘርዝሯል።
አረና ከተመሰረተበት ከ2000 ዓም ጀምሮ ባለፉት 8 ዓመታት ዝናቡ ሃይሉን ጨምሮ አራት አባላት እንደተገደለበት ገልጾ፣ ስማቸውንም ዘርዝሯል። ሟቾቹ አረጋዊ ገ/ዮሃንስ፣ ልጃለም ካልአዩ እንዲሁም ታደሰ አበራ ናቸው።