የአረና ትግራይ መሪዎች ለቅስቀሳ በሄዱበት አዲግራት ተደበደቡ

ጥር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነባሩ የቀድሞው የህወሀት ታይ እና አሁን የአረና ከፍተኛ አመራር አቶ አስገደ ገብረስላሴ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች በመጻፍ የሚታወቀው ና የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር አብረሃ ደስታ እንዲሁም የፓርቲው የአመራር አባል አቶ አምዶም ገ/ስላሴ እሁድ እለት ከአዲግራት ህዝብ ጋር ለመነጋገር ወደ ስፍራው ቢያቀኑም በከተማው የደህንነት ፣ የፖሊስና የቀበሌ ሹሞች የሚመሩ ወጣቶች ድብደባ በመፈጸማቸው ስብሰባውን ማከሄድ ሳይችሉ ቀርተዋል።

መምህር አብርሃ ለኢሳት እንደገለጸው ድብደባው ሆን ተብሎ በመንግስት ሃይሎች የተቀናበረ ነው። ለድብደባው ምክንያት የሆነውም በከተማዋ ውስጥ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም በሚል ነው

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሰማያዊ ፓርቲ  በጎንደር ከተማ ለሚያደርገው ሰልፍ በማስተባበር ላይ የሚገኙት የፓርቲው የአደረጃጀት ኃላፊ ኢንጅነር ጌታነህ ባልቻ፤እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን የፓርቲው የዞን ሰብሰቢ የሆኑት አቶ አግባው ሰጠኝን በፖሊስ መያዛቸውን ፓርቲው አስታውቋል።