ጥቅምት ፭(አምት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ዜጎቹ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫ አልሸባብ በቦሌ አካባቢ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀ መሆኑን አስተማማኝ መረጃ እንደደረሰው ገልጿል።
ኤምባሲው አዲስ መግለጫ እስከሚወጣ ድረስ ዜጎቹ ከሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የማምለኪያ ቦታዎች፣ ከገበያ ቦታዎችና የመዝናኛ ቦታዎች እንዲርቁ መክሯል። ጥቃቱ የሚፈጸምበት ትክክለኛ ቦታ ባይታወቅም ፣ የአሜሪካ ዜጎች የራሳቸውን ደህንነት እንዲጠብቁ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአልሸባብን ዛቻ እንደሚያከሽፈው ገልጿል።
የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት መረጃዎችን ይፋ ያደረገው ዊኪለኪስ ከአመታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት “በአገሪቱ የሽብር አደጋ አለ ለማለት ፈንጅዎችን እንደሚያቀናብር” ይፋ አድርጎ ነበር።
የኢትዮጵያ ጦር ካለፉት 9 አመታት ጀምሮ በሶማሊያ ውስጥ ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ኬንያ ሰራዊት ጋር በጥምረት ከአልሸባብ ጋር እየተዋጋ ቢሆንም፣ እስካሁን አልተሳካለትም። አልሸባብ በእነዚህ ሃይሎች ጥቃት ከሞቃዲሾና ዋና ዋና ከሚባሉ ስትራቴጂያዊ ቦታዎች እንዲለቅ ተገዷል።