(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 14/2010)የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሕጻናትን ከወላጆቻቸው እንዳይነጠሉ የሚያደርግ አዲስ መመሪያ ማውጣታቸው ተሰማ።
ፕሬዝዳንቱ መመሪያውን ያወጡት 2 ሺ 3 መቶ ያህል ሕጻናት ከወላጆቻቸው ተነጥለውና በአጥር ተከልለው እንዲቀመጡ መደረጉ የቀሰቀውን አለምአቀፍ ቁጣ ተከትሎ ነው፡፡
በዚህም መመሪያ መሰረት የተለያዩ ወላጆችና ሕጻናት እንዲገናኙ ተወስኗል።
ድንበራችንን ከሕገወጥ ስደተኞች መጠበቃችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሆኖም ሕጻናትና ወላጆቻቸው በአንድ ላይ እንዲሆኑ እንፈልጋለን ብለዋል ዶናልድ ትራምፕ።
የነበረውን ሁኔታ ሲመለከቱም መደንገጣቸውን ተናግረዋል።
በአለም አቀፍ ደረጃ ቁጣን የቀሰቀሰው ስደተኛ ሕጻናትን ከወላጆቻቸው የመለየቱ እንቅስቃሴ የሰሞኑ አብይ መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወሳል።
ባለፈው አርብ የአሜሪካ የሃገር ውስጥ የደህንነት ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ 1 ሺ 995 ሕጻናት እንዲሁም 1 ሺ 940 ወላጆቻቸው ተለያይተዋል።
እነዚህ ሕገ ወጥ ስደተኞች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሚያዚያ 19/2018 እስከ ግንቦት 31/2018 በአንድ ወር ከ10 ቀናት ጊዜ ውስጥ የገቡ መሆናቸውን ገልጸው ነበር።
የሕጻናቱ ወላጆች አሜሪካ ውስጥ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመግባታቸው እንዲከሰሱ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
ሕጻናቱን ከወላጆቻቸውና ከአሳዳጊዎቻቸው የመለየቱ ስራ የሚሰራውም ሕገ ወጥ ስደተኞቹን ለመክሰስ ከሚደረገው ዝግጅት ጋር የተያያዘ መሆኑም ተገልጾ ነበር።
ለሕገ ወጥ ስደተኞቹ ቅንጣት ትዕግስት የለንም የሚለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፖሊሲ ያስከተለው ይህ ሁኔታ አለም አቀፍ ቁጣን ቀስቅሷል።
የአሜሪካ ታዋቂ ፖለቲከኞች ድምጻቸውን ያሰሙ ሲሆን በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞችም የተቃውሞ ትዕይንቶች ተካሂደዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርምጃውን ከተቃወሙት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በአሜሪካ ምክር ቤት የዲሞክራቲክ ፓርቲው ተጠሪ ናንሲ ፔሎሲ”አሳፋሪ ርምጃ” በማለት ሲያጣጥሉት፣የካሊፎርኒያ ግዛት ሴናተር ሰብአዊ ክብርን የሚነካ ፖሊሲ ሲሉ ለርምጃው መነሻ የሆነውን እቅድ አውግዘዋል።
ከዚህ ሁሉ ውዝግብ በኋላም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አዲስ ትዕዛዝ በማስተላለፍ ወላጆችና 2 ሺ 3 መቶ ሕጻናት እንዲገናኙ ማድረጋቸው ተሰምቷል።