ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-
የአማራ ወጣቶች የጋራ ንቅናቄ በአማራ ክልል ላኩማ ወረዳ ሁለት የሚሊሽያ ሀላፊዎችንና አንድ የወረዳ አስተዳዳሪን በቁጥጥር ስራ ማድረጉን ገለፀ፡፡
ንቅናቄው ሰሞኑን 22 የፖለቲካ አመራሮች በላኩማ ወረዳ በሚገኘው በሰላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ በስብሰባ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ መልቀቁን ገልጾ ሶስቱን አመራሮች ግን አሁንም ድረስ በቁጥጥር ስር አድርጎ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የተያዙት አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ከነበሩት ፓለቲከኞች ዋነኛ እና የአካባቢውን ህብረተሰብ በመበደል የሚታወቁ እንደሆነ ንቅናቄው አመልክቷል፡፡
አቶ አልዩ ጋሹ የላኩማ ወረዳ አስተዳደር ስብሳቢ፣ አቶ አንበሱ በዙ የሰገላ ወረዳ ሚሊሺያ ዘርፍ ሀላፊ፣ እንዲሁም አቶ ኢያና ካሳ የባምበል ወረዳ ሚሊሽያ ዘርፍ ሀላፊ ሶስቱም በቁጥጥር ስር የሚገኙ ሀላፊዎች እንደሆኑ ንቅናቄው ገልጿል፡፡
ይሁንና ኢሳት በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሀላፊዎች ከገለልተኛ ወገን ያገኘው ማረጋገጫ የለም፡፡
ላኩማ ወረዳ ብዙ የሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት ያለባት ስፍራ እንደሆነች የገለጸው ንቅናቄው ከዚህ በፊት የአካባቢውን ሰዎች ሲያጉላላ የነበረ ሀላፊ እርምጃ ተወስዶበት እንደነበር አስታውሷል፡፡
ንቅናቄው በክልሉ ባሉ ህዝቦች ላይ የሚፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሰቃይ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
የጎጃም ዞን ዋና የህወሀት ባለስልጣን በነበሩት አቶ ዳኘ ገብረማርያም ላይ በቅርቡ እርምጃ መወሰዱን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡