በአዲስአበባ ከተማ የማጅራት ገትር ወረርሽኝ በአዲስ መልክ ተቀሰቀሰ

ጥቅምት ፲፭(አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር 2005 አካባቢ ተከስቶ የነበረው ማጅራት ገትር ወረርሽኝ እንደገና በአዲስ መልክ በመቀስቀሱ የክልሉ ጤና ቢሮ ሕዝቡን የመከተብ ስራ ላይ መጠመዱ ተሰማ፡፡

ክትባቱ በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በመሰጠት ላይ ሲሆን ክትባቱን መውሰድ ያለባቸው ደግሞ ዕድሜያቸው ከ30 በታች የሆኑ ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸው ለምን የሚል ጥያቄ አስነስቶአል፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት መንግስት የገጠመውን የመድሃኒት ዕጥረት ለመቅረፍ የወሰደው ዘዴ በዕድሜ ገደብ ክትባቱን መስጠት እንዳስገደደው ጠቁመዋል፡፡

ከአዲስአበባ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ግን የማጅራት ገትር በሽታ ሁሉንም ሰው የሚያጠቃ ቢሆንም ዘጠና በመቶ የሚታየው
ዕድሜያቸው ከ2 አስከ 30 ዓመት ባሉት ላይ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ እድሜያቸው ከ30 በላይ የሆኑት ያልተካተቱት ተጋላጭ ባለመሆናቸው እንጂ መድሃኒት ባለመኖሩ አይደለም ይላል፡፡

የማጅራት ገትር ሕመም በተዋህሲን አማካይነት ተከስቶ የአንጎልን ህብለሰረሰር በተለይ ከራስ ቅል በታች ያለውን የሰውነት ክፍል የሚያጠቃ ሕመም ነው፡፡

በባክቴሪያ አማካይነት የሚከሰተው ማጅራት ገትር በሽታ በወረርሽኝ መልክ
የሚተላለፍ ፣ በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኙ አገራት በ10 ዓመት አንድ ግዜ የሚከሰት ሲሆን በኢትዮጽያ በ8 ኣመት አንድ ጊዜ እንደሚከሰት ከአ/አ ጤና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

በሽታው በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ አማካነት የሚመጣ ሲሆን ዋናው የበሽታ ምልክት የአንገት መቆልመም፣ ትኩሳት፣ብርሃንን ለማየት መቸገር በዋንናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በሕጻናት ላይ አናታቸው አካባቢ የማበጥ፣የማቅለሽለሽ ፣ትኩሳት ፣አእምሮ መሳት፣የቅዥትና የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡