በጋምቤላ ለሞቱ የሰራዊቱ አባላት ካሳ ተከፈለ – ለሞቱ ነዋሪዎች ግን ካሳ አለመከፈሉ ታወቀ

ጥቅምት ፲፭ (አስራ አምስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በቅርቡ በጋምቤላ ክልል ንዌር ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ሚኒኛንግ ከተማ ተካሂዶ በነበረ ግጭት ለሞቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በነብስ ወከፍ 90 ሺህ ብር እንዲከፈል ተወሰነ፡፡ ለሞቱ ሲቪል ሰዎች የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም መቅረቱን ግን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ሚሊሺያዎች እና ነዋሪዎች ከመከላከያ አባላት ጋር ባደረጉት ግጭት ስምንት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሞተው ሰባት መቁሰላቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ከሞቱ እና ከቆሰሉት የመከላከያ አባላት በተጨማሪ ስድስት ነዋሪዎች ለቀናት በዘለቀው ግጭት ተገድለዋል፡፡

የጋምቤላ መስተዳደር ለክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ለሞቱ ስምንት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ለእያንዳንዳቸው 90 ሺህ ብር እንዲከፈል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ለቆሰሉ ሰባት አባላትም ለእያንዳንዳቸው 30 ሺህ ካሳ እንዲከፈል የተወሰነ ሲሆን ለሞቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ምንም የካሳ ክፍያ ሳይፈጸም መቅረቱን የኢሳት ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ለተገደሉት ነዋሪዎች ክፍያ አለመፈጸሙ የሟች ቤተሰቦችን እንዳሳዘነ የገለጹት እማኞች ጉዳዩ በበርካታ ነዋሪዎች ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ለመከላከያ አባላት የተመደበው ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸው እንደማይደርስ የጠቆሙት እማኞች ትዕዛዙ የክልሉን ገንዘብ ከመበዝበር ያለፈ እንደማይሆን ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሳምንት በፊት በንዌር ዞን በተቀሰቀሰ ግጭት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና አፈ-ጉባኤ መገደላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ግጭቱ የተቀሰቀሰው እግር ኳስ ሲመለከቱ በነበሩ ሰዎች መካከል ቢሆንም ነዋሪዎች የፖለቲካ አጀንዳ ሊኖረው እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡