የአማራ ክልል የድንበር ከተሞች ለአጎራባች ክልሎች ሊሰጡ ነው፡፡

መስከረም (ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ኢሳት ከአማራ ክልል ባለስልጣናት ባገኘው መረጃ  የጃን አሞራ፣ የማይጸብሪ አዋሳኝ፣ ራስዳሸንን ጨምሮ የአዲአርቃይን አካባቢዎች ወደ ትግራይ፣ በመተማ በኩል ደግሞ የተወሰነውን ክፍል ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመስጠት ድርድር በመካሄድ ላይ ነው።

ባለስልጣናቱ ቀደም ብለው የህዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ አንዳንድ የወረዳ ባላስልጣናት ጉዳዩን ወደ መድረክ እንድናወጣላቸው ተማጽነዋል።

መንግስት ከአሁን በፊት በአማራ ክልል ስር የነበረውን የመተከል ዞን ለቢኒሻንጉል ጉምዝ ፤ራያና ቆቦ ፤ዳንሻ እና ሁመራ ፤በመተማ በኩል ለሱዳን ፤የመተማ ቀሪው ክፍል ለቤንሻንጉል ፣ በሰሜን ሺዋ በኩል  ለኦሮምያ የልማት እገዛ በሚል መሰጠቱን በማውሳት ፣ አሁንም ተጨማሪ መሬት እየተቆረሰ ክልሎችን ለማስደሰት እየዋለ ነው በማለት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የአንቀጽ 39 ቱርፈቶች የሰጡን ገፀ በረከቶች ናቸው ሲሉ የአማረሩት የድንበር ከተማ ነዋሪዎች፣  “ጨለምተኛ አባት መሬት እየሸጠ ልጆቹን ከእርስት ይነቅላል፡፡ ጨለምተኛ መንግስት አገርን በመሸጥ ዜጎችን ያስደፍራል፡፤ ምንነታቸውን ያሳጣል መንግስትም ማንነታችን እየነጠቀን ነው ሲሉ” ገልጸዋል።

ሁኔታው ያበሳጫቸው ነዋሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ድርጅቶች ጉዳዩን አጽንዎት ሰጥተው ሊያዩት ይገባል ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትግርኛን ቋንቋ በአማራ ክልል ተማሪዎች እንዲማሩት ለማድረግ ታስቦ በጎንደር በተካሄደው የፓይለት ጥናት ህዝባዊ ተቃውሞ በማስነሳቱ እንዲቆም ተደርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ባየ ይማም በቅርቡ በአቀረቡት ጥናት የመንግስት ቋንቋ አጠቃቀም ‘የህዝብን ጉዳይ በህዝብ ቋንቋ’ የሚለውን መርህ የተከተለ ባለመሆኑ ህዝቡ ማግኘት ያለበትን መልእክት በትክክል እያገኘ፤ ለለውጥም እየተነሳሳ አይደለም ብለዋል፡፡ ባጭር ቃል በዚህ አይነት ቋንቋ የሕዝብን አእምሮ መቀየር እንደማይቻል የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ባለስልጣናቱ  የአማረኛ ቋንቋ እንዲጠፋ የበኩላቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል፡፡

“ሀገራችን የቋንቋ ፖሊሲና የአጠቃቀም ደንብ ወይም ስርዓት እስካሁን የላትም፡፤ እስካሁን ድረስ ከህገመንግስታዊ የመብት ማረጋገጫ አንቀጾች ያለፈ፣ ቋንቋን እንደ ማንኛውም የሀገር ሀብት በእቅድ የሚያሳድግ፣ የሚቆጣጠር፣ አጠቃቀሙን ስርዓት የሚያሲዝ ፖሊሲና ዝርዝር ደንብ  የለንም፡፡ ባለመኖሩም ሁሉም እንደፈለገ የሚተረጉምበት፣ የሚጽፍበት፣ የሚያሰራጭበት ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህ ሊቆምና ቋንቋዎቻችን በዕቅድ ሊያድጉና ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል” ሲሉ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።

ፕሮፊሰር ባየ ይማም ለቋንቋው ድክመት  የመንግስት ባለስላጣናት ተጠያቂ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አማርኛ ቋንቋ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ መሆኑ እየታወቀ ክልሎች በፍፁም ጥላቻ እንዲያድርባቸው እንዲሁም  ክፍል ውስጥ ገብተው የመማርን መብት ለተወላጆች ብቻ ትቻለሁ በማለት የአማርኛ ትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ፤ በትግራይ ፤ ኦሮምያ፤እና ደቡብ ልልኦች ክፍት ይሆናሉ።

ተማሪዎች በቋንቋ ትምህርት በሚመዱበበት ወቅትም በአማርኛ ቋንቋ የሚሰጡ ደጋፊ ትምህርቶችን ላለመማር አሰጣ አገባ እንደሚገቡ ታውቁዋል፡፡

በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል እና ሶማሊ ክልሎች የክልሎቹን ቋንቋ የማይናገሩ ተማሪዎች ተመርቀው ስራ ለማግኘት አይችሉም። በመሆኑም ከአማራ ክልል የሚመጡ ተማሪዎች ከክልላቸው፣ ከአዲስ አበባ እና ከደቡብ ክልል ውጭ በሌሎች ክልሎች ተቀጥረው ለመስራት እየተቸገሩ ነው።

አንዳንድ ልዩ ችሎታ ያላቸው ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው ለመስራት ካልሆነ በስተቀር የአማራ ክልል ተማሪዎች ስራ ለመያዝ እንደሚቸገሩ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ግን አማርኛ የሚችል የማንኛውም ክልል ተወላጅ በአማራ ክልል ተወዳድሮ ስራ የመያዝ መብቱ የተጠበቀ ነው።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደልብ ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብት በእጅጉ ተገድቧል።