ዋልያዎች፦” የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድንን ካሸነፍን እንዲሚሰጠን ቃል የተገባልን ቦነስ ገንዘብ ያንሰናል” በማለት ቅር መሰኘታቸው ተገለጸ።

መስከረም (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ሱፐር ኤግልስን ካሸነፉ መንግስት  እንደሚሰጣቸው ቃል የገባላቸው ቦነስ በቂ እንዳልሆነና ስሜታቸውን የሚያነሣሳ እንዳልሆነ ነው  ተጫዋቾቹ የተናገሩት።

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከቀናት በፊት የ22ቱን ተጫዋቾች ስም ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ በቡድኑ ውስጥ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆነው ጌታነህ ከበደ በጉዳት ምክንያት በቡድኑ ውስጥ አልተካተተም።

በቀራቸው የደርሶ መልስ ጨዋታ ናይጀሪያን አሸንፈው ለዓለም ዋንጫ ካለፉ የሚሰጣቸው ቦነስ ምን ያህል እንደሆነ ዝርዝሩ በይፋ ባይታወቅም፤አብዛኞቹ ተጫዋቾች ግን ውስጥ ለውስጥ የቦነስ መጠን እንደሚያንሳቸውና ከዚያ በላይ እንደሚገባቸው እየተናገሩ ነው።

“ቃል የተገባልን ነገር የሚያሳየው መንግስት ለኛና ለውድድሩ የሰጠው ትኩረት ዝቅ ያለ መሆኑን ነው። ካሸነፍን ከዚህ በላይ ሊደረግልን ይገባል” ብሏል- በቡድኑ ምርጫ ከተካተቱት ተጫዋቾች አንዱ።

ይሁንና በሱዳን ለአል አህሊ እየተጫዎተ ያለው አዲስ ህንፃ፣በሊቢያ ለአል ኢትሀድ እየተጫዎተ ያለው ሽመልስ በቀለ እና በ እስራኤል እየተጫዎተ ያለው አዲስ መገርሳ ሰሞኑን ቡድኑን መቀላቀላቸውን ተከትሎ የተጫዋቾቹ መንፈስ መነቃቃቱ ተዘግቧል።