ሐምሌ ፳፭(ሃያ አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የ2005 የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ሪፖርት የህዝብና የመንግስት ሃብት አጠቃቀም አሳሳቢ የሆነ ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡
መስሪያ ቤቱ በመጠናቀቅ ላይ ባለው አመት በኢንዱስትሪ ከተማ ልማት ቢሮ ፤ በገጠር መንገዶች ባለስልጣን ፤ በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጅንሲ ፤በባህል እና ቱሪዝም ና ፓርኮች ልማት ቢሮ የክዋኔ ኦዲት ሰርቷል። 251 ሚሊየን ብር ወጪ ቢደረግም መረጃ አልቀረበባቸውም ሲል ሪፖርት አመልክቷል፡
የቢሮው ም/ ዋና ኦዲተር አቶ ስመኝ ካሴ እንዳሉት በአምስት ዞኖች በናሙና በተመረጡ አስራ አምስት የመንግስት ግንባታዎች የክዋኔ ኦዲት ተደርጎ አብዛኛቹ በተፈቀደላቸው ዲዛይን የስራ ዝርዝር እያከናወኑ አይደለም፡፡ በዚህም በቢሊዩን የሚቆጠር ብር ለግለሰቦች ገቢ እየሆነ ነው፡፡
በኦዲቱ መሰረትም 11 የህንጻ ግንባታዎች ዲዛይናቸውና የስራ ዝርዝራቸው ያልተሟላ ና ያልተጣጣመ ሁኖ ለባለስልጣናት የግል ሃብት ሲውል ተጠያቂ ሲሆኑ አልታየም፡፡ በዚህም በከፋ ሁኔታ ለችግር እየተጋለጡ ነው፡፡
አቶ ስመኝ ካሴ ባቀረቡት ሪፖርትም 10 መስሪያ ቤቶችም አግባብ ያልሆነ ክፍያ በመክፈል በድምር በቢሊዩን የሚቆጠር ብር አባክነዋል፡፡
ከአመራሮችና ጋር ሺርክና በመፍጠር ደረጃቸውን ባልጠበቁ የህንጻ ቁሳቁሶች መገንባት እና አላአግባብ ክፍያ መፈጸም ፤ የቁጥጥር ስርዓት ድክመት ፤የህንጻ ቁሳቁሶች መጥፋት እና መሰል ችግሮች በሪፖርቱ የተመለከቱ ናቸው፡፡ በዚህም ባጠፉት አካላት ላይ ምንም አይነት አካላት እርምጃ አልተወሰደም፡፡
የኢንዱስትሪ ከተማ ልማት ቢሮ በግኝቶች ላይ ተገቢው የማስተካካያ እርምጃ እንዲወሰድ እና ለተሰጠው የኦዲት አሰተያየት በሪፖርቱ ላይ ዝርዝር ምላሺ ለመስጠት የተቆጣጣሪነት ድርሻው ከሌሎች የህንጻ አሰሪ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ድርሻ እና ሃላፊነት ጋር በመቀላለቀሉ ለይቶ አላሳየም በማለት ሪፖርቱን በግብኣትነት ወስዶ እየተጠቀመበት መሆኑን ከመግለጽ በስተቀር በግኝቶች ላይ ሰለተወሰደው እርምጃ የሚያሳይ ዝርዝር ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡
የክልሉ ኦዲተር መስሪያ ቤት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የስራ እንቅስቃሴን አስመልክቶ በናሙናነት በተመረጡ የደቡብ ወሎና ምስራቅ ጎጃም በደብረማርቆስ እና ደሴ መቶ በመቶ ከተቀረጸው ዓላማ አንጻር ምንም ስኬት ሳያስመዘግቡ በብድር የተወሰደው በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተግባር ላይ ሳይውል ቀርቷል፡፡
በአማራ ክልል የገጠር መንገዶችም ባለስልጣን በግዥ እና ኪራይ ሰበብ ከፍተኛ ወጭ እና የሃብት ብክነት ተመዝግቦዋል፡፡
በአጠቃላይ በሪፖርቱ የተመዘገበው የመንግስት ሃብት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ የሆነ የአሰራር ብለሹነት እንዳለ አሳይቱዋል፡፡ ምክር ቤቱንም ያነጋገረ ጉዳይ ነው፡፡
የምክር ቤት አባላትም ” የመንግስት ሀብትና ንብረት ያለ አግባብ እየባከነ ነው፣ ዋና ኦዲተር መ/ቤቱ ጉዳዩን ማስረጃ በማስደገፍ አስቀምጦታል ሆኖም ግን ችግሩ ከተፈጠረ በኃላ ምንም እርምጃ ሲወሰድ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ጉደለቱ ብቻ ተነግሮ በዚያው ይቆማል፡፡” በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ኢሳት የክልሉ ዋና ኦዲት ቢሮን ጠቅሶ በአማራ ክልል ከ2001- 2004 ዓ.ም 67 በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችን የያዙ በገንዘብ የማይገመቱ ቅርሶች መዘርፋቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡