የአማራ ክልል ተወላጆች የተባረሩት በህገወጥ መንገድ ስለገቡ ነው በማለት ባለስልጣናት ተናገሩ

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ለዓመታት በቤንሻንጉል ክልል ይኖሩ የነበሩ  የአማራ ክልል ተወላጆች ፦“በሕገወጥ መንገድ ስለገቡ ወደመጡበት መመለስ አለባቸው” ተብለው ከይዞታቸው መፈናቀላቸውን አዲስ አድማስ ዘገበ።

በሚኖሩበት አካባቢ የእርሻ ቦታ በማጣታቸው የተሻለ ሥራ ለመፈለግ  ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሶ ወረዳ በመሄድ ኑራቸውን ሲመሩ የቆዩ  በርካታ ሰዎች በወረዳው ባለሥልጣናትና ፖሊሶች፤ ሰብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ነው ለጋዜጣው የገለፁት።

ስለ ጉዳዬ የተጠየቁት የያሶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ሻምበል ዳኛ በበኩላቸው ‹‹ከየትኛውም ክልል የሚመጡ ሰዎች ለወረዳው ካላሳወቁና ካላስፈቀዱ ሕገወጥ በመሆናቸው ወደ የመጡበት እንዲመለሱ ስምምነት ላይ ደርሰናል›› ብለዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ግን ፤ ካለፉት ስምንት ዓመታት ጀምሮ ይኖሩበት ከነበረው ክልል የመሸኛ ደብዳቤ አምጥተው በያሶ ወረዳና በየቀበሌዎቹ የነዋሪነት መታወቂያ ተሰጥቷቸው ነው ጎጆ ቀልሰው ሲኖሩ የቆዩት።

ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ በቅርቡ “ከሌላ ቦታ መጥታችሁ እየሠራችሁ የአካባቢውን ተወላጅ ሰነፍ አደረጋችሁት” በሚል ምክኒያት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ሳይሰበስቡ ከክልሉ እንዲወጡ መደረጋቸውን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ፡፡

በያሶ ወረዳ ውስጥ የከተማ ነዋሪነትና የንግድ ፈቃድ በማውጣት ላለፉት ሰባት ዓመታት በሥራ ላይ መቆየታቸውን የጠቀሱ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ ግለሰብ፤ መታወቂያቸውና ቀደም ሲል ይኖሩበት ከነበረው ክልል ያመጡት መሸኛ ደብዳቤ ተወስዶ እንደተቀደደባቸው፤ እንዲሁም በከተማው የሠሩትን ቤት መላ እስኪያስይዙና ንብረታቸውን እስኪሰበስቡ ድረስ ጊዜ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም፤ ‹‹ቤትና ንብረቱ የሚገባው ለወረዳው ነው›› በሚል ወረዳውን ለቀው እንዲወጡ በመገደዳቸው በከተማው አቅራቢያ በሚገኝ ስፍራ ተደብቀው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማይ ዞን በያሶ ወረዳ ውስጥ በሀሎ ትክሻ፣ በሆኒ፣በሊጐ፣ በባብርኮ፣ በሻብቲ፣ በድልድል፣ በቲኒጆ መጢ እና በመሰል ቀበሌዎች በግምት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ከአማራ ክልል የመጡ ሰዎች እንደሚገኙ  ግለሰቡ ገልጸዋል።

እንደማንኛውም ዜጋ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ሠርቶ የመኖር መብታቸውን መሠረት አድርገው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተሻለ ሥራ ፍለጋ መሄዳቸውንና ሕገወጥ ሰፈራ አለማድረጋቸውን የጠቀሱት ግለሰቡ፤ በደሉን እያደረሱባቸው ያሉት የወረዳው ባለሥልጣናት በመሆናቸው አቤት የሚሉበት ቦታ ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ቤተሰባቸውን እና ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ ከየቀበሌው እየተያዙ በያሶ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ የታሠሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም አጋልጠዋል፡፡

“የክልሉ ነዋሪ ወዶንና ተቀብሎን በሰላም ነበር የምንኖረው” የሚሉት የሀሎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ሌላው አርሶ አደር በበኩላቸው፤የመኖሪያ ቤት ለመሥራት ሳይቀር የክልሉ ተወላጆች መሬት ቆርሰው እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል፡፡

ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ግን ጐጐታ በተባለ ቀበሌ ከአማራ ክልል የመጡ 43 ሰዎች እንዲሁም በሀሎ ሙከአርባ ቀበሌ የ25 ሰዎች መታወቂያ ተቀዳዶ ሲጣል መመልከታቸውን፣ ከተቀደዱት መታወቂያዎች አንዱ የእርሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንደሚሉት የጉሙዝ ተወላጅ ከሆኑት ባለመሬቶች አንድ ገበሬ በጉልበቱ አርሶ 20 ኩንታል እህል ቢያመርት፤ 10ሩን ለባለመሬቱ እኩል አካፍሎ በስምምነት ሲኖሩ ነበር፡፡

“እስከአሁን በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ከታሠሩት በርካታ ሰዎች በተጨማሪ በመኪና ተጭነው ነቀምትና ጊንቢ የተወሰዱት ሰዎች ጉዳይ አስጨንቆናል” ያሉት ሌላው ግለሰብ ለታሠሩ ወገኖቻቸው ስንቅ ሊያቀብሉ የሚሄዱትም በዚያው እየተያዙ እንደሚታሠሩ ተናግረዋል፡፡

ስንቅ ሊያቀብሉ በመሄዳቸው ሦስት ቀን ታስረው እንደተለቀቁ የተናገሩት እኚህ ግለሰብ “ከክልላችን መሸኛ ደብዳቤ አምጥተን ሕገ-ወጥ ናችሁ የምንባለው ፓስፖርት ማውጣት ነበረብን ወይ?” በማለት ይጠይቃሉ፡፡

‹‹በኖርንባቸው ሰባትና ስምንት ዓመታት ሠርተን ለመለወጥ ከማሰብ በስተቀር በነዋሪውም ሆነ በአካባቢው ላይ ያደረስነው አንዳችም ችግር የለም” የሚሉት እኚህ ግለሰብ ‹‹ውጡ ከተባልንም ንብረታችንን እስክንሰበስብ ጊዜ ይሰጠን፡፡ የአማራ ክልላዊ መንግሥትም ቦታ ይሰጠን›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የዜጐች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን በተለከተ አስተያየታቸውን የሰቱት የሕግ ባለሞያ አቶ ግዛው ለገሠ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 32 “የመዘዋወር ነፃነት” በሚል ርእስ ስር ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ አገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ፤ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመኖርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከአገር የመውጣት መብት እንዳለው መደንገጉን ገልፀዋል፡፡

ኢሳት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ስለተፈናቀሉ ሰዎች በባህርዳር የሚገኙ ተፈናቃዮችን አነጋግሮ ዘገባ መስራቱ ይታወሳል።