ሜድሮክ ወርቅ እና ሌሎችም የሼክ አላሙዲ ድርጅቶች የታክስ ጥያቄ ተነሳባቸው

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ለመንግስት ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው በኢትዮጵያ ውስጥ ከህወሀት ኩባንያ ከሆነው ኢፈርት በመቀጠል ሁለተኛ የሆነው የሼክ ሙሀመድ አላሙዲ ንብረት ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለመንግስት መክፈል የነበረበትን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ክፍያ አላስገባም።

ኩባንያው ከሚያስታድራቸው ሆቴሎች ጋር በተያያዘ 632 ሚሊዮን ብር እዳ እንዳለበት ጋዜጣው ዘግቧል።

ሚድሮክ ገንዘቡን በአንድ ወር ውስጥ እንዲያስገባ ትእዛዝ እንደደረሰው የኩባንያውን ምንጮች ዋቢ በማድረግ ጋዜጣው ዘግቧል።

በሚድሮክ ኢትዮጵያ ስር ያሉ ሚድሮክ ወርቅ፣ ናሽናል ማይኒንግ፣ ፋርማኪዩር ኩባንያ፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን እና ሚድሮክ የትምህርት እና ስልጠና ኢንስቲቲዩት ባለፉት 2 አመታት የትርፍ ግብር ሪፖርት ዜሮ ሆኖ መገኘቱም ተዘግቧል። 

 ጋዜጣው ያነጋገራቸው አንድ የድርጅቱ ሰራተኛ የተጠቀሱት ኩባንያዎች የትርፍ ግብር ዜሮ ነው መባሉ አስደንግጧቸዋል። ‹‹በአገሪቱ ውስጥ በመሥራት ላይ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች በትርፍ ግብር መልክ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመንግሥት ፈሰስ ሲያደርጉ እነዚህ ትላልቅ ኩባንያዎች አላተረፉም ሲባል ለመስማት ይከብዳል” በማለት ግለሰቡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጉዳዩን በማስመልከት ተጨማሪ መረጃ ለማሰባሰብ ወደ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል።

ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለገደንቢ የወርቅ ማእድንን ከኢትዮጵያ መንግስት እጅግ በርካሽ ዋጋ ከ16 አመታት በፊት መግዛቱ ይታወቃል። ኩባንያው ለረጅም ጊዜ ከወርቅ ሽያጭ ትርፍ አላገኘሁም በማለት 2 በመቶ ብቻ የሮያሊቲ  ክፍያ እየከፈለ  ቆይቷል።

ከምርጫ 97 በሁዋላ ህዝቡ ስለ ወርቅ ማእድኑ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ኩባንያው ከ98 እስከ 2004 ባሉት አመታት 772 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር፣ 241 ሚሊዮን ብር የሮያሊቲ እና 4 ሚሊዮን ብር የሰራተኛ ግብር መክፈሉን አስታውቋል።

ክፍያው የተፈጸመው በአምስት አመታት ውስጥ ለተከናወነው የወርቅ ሽያጭ ብቻ ሲሆን ፣ ላለፉት 11 አመታት ለተካሄደው የወርቅ ሽያጭ ኩባንያው ግብር ያልከፈለበት ምክንያት እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሎአል። መንግስትም በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሲሰጥ አይሰማም።

ባለፉት 3 አመታት በአለም ላይ የታየው የወርቅ ዋጋ መናር ሚድሮክ ኢትዮጵያ ከወርቅ ሽያጭ ከፍተኛ ሀብት እንዲያጋብስ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከሁለት ወር በፊት የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ያስገኙ ድርጅቶች በሚል 175 ኩባንያዎችን አወዳድሮ ፣ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ 100 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በማስገባት አንደኛ ሆኖ መሸለሙ ይታወሳል። በዚያው አመት ግን ድርጅቱ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ ማከናወኑን አስታውቆ ነበር።

በአለፉት አስራ ስድስት አመታት ኩባንያው 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወርቅ ለገባያ አቅርቧል። ይሁን እንጅ ኩባንያው እስካሁን ለመንግስት ያስገባው የትርፍ ግብር ገ ከ40 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥም።

ሚድሮክ የሚያወጣው ወርቅ የሚጣራው ስዊዘርላንድ ውስጥ ነው።

ሼክ ሙሀመድ አላሙዲ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ እንደሚናገሩ ይታወቃል። ለድርጅቱም ከፍተና የሆነ ገንዘብ ይለግሳሉ። ሰሞኑን በተካሄደው የኢህአዴግ ጉባኤም የክብር እንግዳ ሆነው ተጋብዘዋል። አቶ በረከት ስምኦን የጻፉትን መጽሀፍ ያሳተሙላቸው ሼክ አላሙዲን ሲሆኑ ፣ አቶ በረከት ከምርጫ 97 በሁዋላ ታመው በነበረበት ወቅት ያሳከሙዋቸው ሼክ አላሙዲን መሆናቸውን በወቅቱ ተናግረው ነበር። በርካታ የቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣናት  ስራቸውን እየለቀቁ ሚድሮክ ኢትዮጵያ መቀጠራቸው ይታወቃል።