(ኢሳት ዜና–ሕዳር 25/2010)
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች አካባቢውን እየለቀቁ ወደ ሃዋሳና አዲስ አበባ እየሄዱ መሆናቸው ተነገረ።
በአካባቢው ሃብትና ንብረት አፍርተው ይኖሩ የነበሩ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ስፍራውን ለመልቀቅ የተገደዱት በጌዲዮ ተወላጅ አመራሮች ጫና እየደረገባቸው በመሆኑ ነው ሲሉ የኢሳት ምንቾች ገጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የአካባቢውን ሕዝብ ሰሞኑን ሰብስበው የጌዲዮ አመራሮችን መውቀሳቸው ተነግሯል።
የጌዲዮ ዞን አስተዳደር አመራሮች በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ይኖሩ የነበሩ ሌሎች ብሔሮችን ሲበድሉና ሲያንገላቱ መቆየታቸው ይነገራል።
በቋንቋ ላይ በተመሰረተው ፌደራሊዝም ለስልጣን የበቁት እነዚሁ የደኢህዴን ካድሬዎች በዲላ፣በይርጋጨፌ፣ወናጎና መሰል አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩትን የኦሮሞና የአማራ ብሄረሰቦች ወደ ሌላ አካባቢዎች እያሳደዱዋቸው መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በጌዲኦ ዞን ሀብትና ንብረት አፍርተው ይኖሩ የነበሩት የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ጥሪታቸውን ትተው ወደ ሃዋሳና አዲስ አበባ መሰደዳቸው ነው የተነገረው።
አንዳንዶቹም የቡና ልማት የነበራቸውና ጥረውና ግረው ሃብት ያፈሩ መሆናቸውንም የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።
እዚያው የቀሩትም የሌሎች ብሔረሰብ አባላት በስጋት ውስጥ መሆናቸውም ታውቋል።
በጌዲዮ ዞን ያለው ሁኔታ ያሳሰባቸው የአገዛዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው ሰሞኑን አወያይተዋል።
በዚሁም ሌሎች ብሔረሰቦች አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ ያበቋቸው የጌዲዮ ዞን አስተዳደር አመራሮች ናቸው ብለዋል።
“እናንተ የከሳ ጸጉራም በጎች ናችሁ” በማለት “አላችሁ ስትባሉ የሌላችሁ ናችሁ”ሲሉም መውቀሳቸው ነው የተነገረው።
በህገመንግስቱ ዜጎች የትም የመኖር መብት አላቸው ቢሉም ታዛቢዎች ግን ይህን ስርአት የፈጠረው ማነው ሲሉ የአቶ ሃይለማርያምን አባባል አጣጥለውታል።
በጌዲዮ ዞን ያሉ አመራሮች ወደ ስልጣን የወጡት “ይህ አካባቢ የእናንተ ብቻ ነው፣ከእናንተ በላይ ማንም የለም እየተባሉ ሌሎችን ብሔረሰቦች እንዲያጣጥሉ በአገዛዙ ሲደገፉና ሲበረታቱ እንደነበር የአካባቢው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።