(ኢሳት ዜና – ሃምሌ 3 , 2009 )
የኦሮምያና የአማራ እግር ኳስ ክለቦች ደጋፊዎች በባህርዳር ስታዲየም የጋራ ትብብር ባማሳየት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ ህውሃት / አገዛዝን አወገዙ ።
የባህርዳር ከተማ ክለብና የኦሮምያ ለገጣፎ እንዲሁም የአማራ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት / አውስኮድ / ከሱሉልታ ጋር ሲጫወቱ የየክለቦቹ ደጋፊዎች በወዳጅነት መንፈስ በጋራ ሲጨፍሩ ታይተዋል::
በውድድሩ በባህርዳር ከተማና ለገጣፎ ተጫውተው 0 ለ 0 ሲለያዩ ሱሉልታ አውስኮድ ቡድን 1 ለባዶ አሸንፏል ።
በዚሁም ጊዜ በባህርዳር አጼ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተካሄዱ ጨዋታዎች የአማራና የኦሮምያ ደጋፊዎች በትብብር ስሜት ሆነው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ / ህውሃትን /አገዛዝ አውግዘዋል ።
ደጋፊዎቹ የክለባቸውን አርማና ኮከብ የሌለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ይዘው የኦሮሞና የአማራ ህዝብ አንድ መሆኑን የሚያሳዩ ዜማዎችን ሲያሰሙ ውለዋል ።
የአማራና የኦሮምያ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ህብረታቸውን በወዳጅነት ስሜት በጭፈራ ሲያሳዩና ህውሃትን ሲያወግዙ በፌዴራል ፖሊሶች ከመከበባቸው ውጪ የደረሰባቸው ጉዳት የለም ።
በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ በተቀሰቀሰበት ጊዜ የኦሮሞ ደም ፥ ደሜ ነው በማለት በጎንደርና በባህርዳር ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች ህብረታቸውንና አጋርነታቸውን ማሳየታቸው ይታወሳል ።