የአልጀዚራን ድረ-ገጽ በኢትዮጵያ እንዳይታይ ታገደ

መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት የ አልጀዚራን እንግሊዝኛ እና ዐረብኛ ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ማገዱን አልጀዚራ ዘገበ።

ድርጊቱ፤የ ኢትዮጵያ መንግስት እንደ አዲስ እያደረበት ከመጣው ፍርሀት አኳያ ሚዲያዎችን ጸጥ ለማሰኘት እየወሰደ ያለው እርምጃ  አካል ነው ብሏል- አልጀዚራ።

አልጀዚራ ከጎግል የተቀበላቸው ዳታዎች  እንደሚያሳዩት፤ባለፈው ሀምሌ ወር እስከ 50000 ደርሶ የነበረው  እንግሊዝኛ ድረ-ገፁን የሚጎበኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በመስከረም ወር በአስደንጋጭ ሁኔታ  ወደ 114 አሽቆልቁሏል።

በተመሣሳይ በሀምሌ ወር 5371 ደርሶ የነበረው የ አረብኛው ድረ-ገጽ ጎብኝዎች ቁጥር በመስከረም ወደ 2 ወርዷል።

ለደህንነቱ ሲል ስሙን መግለጽ ያልፈለገ አንድ የብሎግ አዘጋጅ  የሙስሊሞች ተቃውሞ በዜና አውታሩ ሽፋን ማግኘት ከጀመረበት ጊዚ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግስት አፈናውን በአልጀዚራ ላይ ትኩረት ሰጥቶና አጠናክሮ እንደቀጠለበት መናገሩን አልጀዚራ ዘግቧል።

ስለጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን የሚዲያ ተቋሙ ገልጿል።

በአገር ውስጥ የሚታተሙ የግል ፕሬሶችን ከህትመት ውጪ በማድረግና ጋዜጠኞቹን በማሰር እና በማሳደድ ያልረካው የ ኢትዮጵያ መንግስት በውጪ አገር የሚዘጋጁ ድረ-ገፆችን ለማገድ እና የ ኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎችን ለማገድ ከፍ ያለ ገንዘብ እንደሚያፈስ ይታወቃል።