የአልሸባብ ሚሊሻዎች በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ሀሰት ነው አለ

መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የአልሸባብ ሚሊሻዎች  ሶማሊያ በሚገኘው  የኢትዮጵያ ጦር ላይ በከፈቱት ጥቃት ከፍ ያለ ጉዳት እንዳደረሱ በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን የተሰራጨውን ዜና ውሸት ነው ስትል ኢትዮጵያ  አስተባበለች።

አልሸባብ በበኩሉ የማረካቸውን  የኢትዮጵያ ወታደሮች የድምፅ መረጃ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ  በማስታወቅ፤ ኢትዮጵያ የደረሰባትን ኪሳራ ልታስተባብል እንደማትችል ገልጿል።

አልሸባብ ባለፈው ማክሰኞ በኢትዮጵያ ጦር ላይ መንገድ ዘግቶ በወሰደው ድንገተኛ የማጥቃት እርምጃ፤ በርካታ የኢትዮጵያ ወታደሮች እንደተገደሉ ቢቢሲን፣አልጀዚራንና ሲ.ኤን.ኤንን ጨምሮ በርካታ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች በስፍራው ያሉ ወኪሎቻቸውን በመጥቀስ ነው የዘገቡት።

ለአራት ሰዓታት የቆየ ነው በተባለው ውጊያ ኢትዮጵያ ከሰባ በላይ ወታደሮቿን እንዳጣች የአልሸባብ ቃል አቀባይ  መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር  ዉጊያው  ከተካሄደ ከስድስት ቀናት በሁዋላ ትናንት ማምሻውን ለውጪ መገናኛ ብዙሀን በሰጠው  መግለጫ ፤አልሸባብ  በኢትዮጵያ ጦር ላይ አደረሰ የተባለው ጥቃት ውሸት ነው በማለት አስተባብሏል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የአልሸባብ ተዋጊዎች ከ ኢትዮጵያ ጦር  ቁጥጥር  ውጪ በሆነች አነስተኛ ቦታ ላይ  ድንገት ጦርነት ቢከፍቱም፤ሠራዊቱ  በወሰደው የአፀፋ ጥቃት ብዙ የአልሸባብ ተዋጊዎች እንደተገደሉና ቀሪዎቹም ሸሽተው እንዳመለጡ  ለሮይተርስ ተናግረዋል።

“የውጊያው ቦታ በአልሸባብ ተዋጊዎች ሬሳ ተሞልቷል”ሲሉም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አክለዋል።

የዓይን ምስክሮችና የበርካታ ብዙሀን መገናኛ ወኪሎች ግን እያሉ ያሉት ግን፤ ከአምባሳደር ዲና ፍፁም ተቃራኒ ነው።

ኢትዮጵያ ጦሯን በሚያዚያ ወር መጨረሻ ለማውጣት ባስታወቀችበት ዋዜማ በአክራሪው አልሸባብ  ከባድ ጥቃት እንደደረሰባት ነው ተጨባጭ መረጃዎች የሚያመለክቱት።

እንደ መገናኛ ብዙሀኑ ዘገባ፤ የኢትዮጵያ ጦር ዳግም ወደ ሶማሊያ ከገባ ካለፈው ህዳር ወዲህ፤ ከባድ ዉጊያ ሲያጋጥመው ይህ የመጀመሪያው ነው።

አልሸባብ በበኩሉ በውጊያው የማረካቸውን የኢትዮጵያ ወታደሮች  ድምጽ አሰምቷል።

ስማቸው ታደሰ እና አበራ እንደሚባልና በአልሸባብ ተዋጊዎች እንደተማረኩ የገለጹት እነዚህ ወታደሮች፤ በውጊውው በርካታ ጓደኞቻቸውን እንዳጡ ሲናገሩ ይሰማሉ።

ሙሉ ቃለ-ምልልሳቸውን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አልሸባብ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በ 2006 ወደ ሶማሊያ ገብታ ባካሄደችው ጦርነት በርካታ ወታደሮች እንደሞቱመዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide