ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ላለፉት 8 አመታት የ11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸውን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰሙ የነበሩት አቶ መለስ፣ ዛሬ 99 ነጥብ ስድስት በመቶ የአንድ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት የፓርላማ ውሎ የአገሪቱ ፈታኝ እና ዋነኛው ችግር የኑሮ ውድነቱ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ መለስ ይህን የተናገሩት “መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰድኩ ነው ቢልም የኑሮ ውድነቱ ግን እየባሰ፣ የምግብ ዋጋ እየጨመረ እና ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል እየተጎዳ ነው” የሚል ጥያቄ ከቀረበላቸው በሁዋላ ነው። አቶ መለስ የኑሮ ውድነቱ የአገሪቱ አንገብጋቢው ችግር መሆኑን አምነው፣ ችግሩ የተፈጠረው በአለም ገበያ መዋዠቅ ፣ የጅምላ ንግድ ስርጭቱ በሞኖፖል መያዝ፣ የገንዘብ አቅርቦት መጨመርና የዋጋ ትንበያ በመበራከቱ መሆኑን ገልጠዋል። መንግስት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ገንዘብ ከብሄራዊ ባንክ እንዳይበደር ማድረጉን፣ ከጅምላ ነጋዴዎች ጋር በመነጋጋርና ስርጭቱ እንዲስተካከል ለማድረግ ጥረት ማድረጉን፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱን ለመቀነስ መወሰኑን እና ሌሎች እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
የስርጭት ስርአቱን ለማስተካካል ከነጋዴዎች ጋር ለመነጋጋር ጥረት ቢደረግም ነጋዴዎች ግን የመንግስትን አማራጭ ለመቀበልና ለመተባባር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ መንግስት ስኳርና ዘይት የመሳሰሉትን ገዝቶ ለማከፋፈል ተገዷል ብለዋል። በአሁኑ ጊዜ በቂ የሚባል ስኳርና ዘይት ከውጭ አገር ተገዝቶ መምጣቱንም አቶ መለስ አስረድተዋል። በአለፈው የካቲት ወር የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የገለጡት አቶ መለስ ይህም የሆነበት ምክንያት የበልግ ዝናብ ስላልነበረ ነው ሲሉ አክለዋል። ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ከውጭ ተገዝቶ ለህዝቡ እየተከፋፋለ መሆኑንም ገልጠዋል። አቶ መለስ የዋጋ ግሽበቱ በሰኔ ወር ወደ አንድ አሀዝ ይገባል ብለው የተነጋሩት ስህተት እንደነበርና አሁን በሚታየው ሁኔታ በሰኔ ወር ወደ አንድ ዲጂት ለማውረድ እንደማይቻል ገልጠዋል።
አቶ መለስ የአለምን የገበያ መዋዠቅ ለመቆጣጠር ሸቀጦች በአገር ውስጥ የሚመረቱበትን መንገድ ማፈላላግ ተመራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አንድ በአገር ውስጥ የሚኖሩ የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ መለስ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት አገሪቱ በዚህን ያክል መጠን አድጋለች እያሉ ቢናገሩ አሁን ከሚታየው የኑሮ ውድነት ጋር ህዝቡ የሚቀበለው አለመሆኑን በመረዳታቸው በችግሮቹ ዙሪያ ላይ ትኩረት አድርገው ለመናገር መምረጣቸውን ገልጠዋል። የኑሮ ውድነቱ መንስኤ በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ ከፍላጎት ጋር ሊመጥን የሚችል በተለይም በቂ የግብርና ምርት ሊመረት ባለመቻሉ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ስንዴ ከውጭ ገዝቶ ማስገባት በቂ ምርት በአገር ውስጥ አለመመረቱን የሚያሳይ እንጅ ከአለም ገበያ መዋዠቅ ወይም ከስርጭት ጋር የሚያያዝነው ነገር የለም ሲሉ አክለዋል። ነጋዴዎች በቂ የእህል ክምችት ቢናራቸው ኖሮ መንግስት አስገድዶ ወደ ገበያ እንዲያቀርቡት ለማድረግ የሚሳነው አልነበረም በማለት የሚገልጡት ባለሙያው የኑሮ ውድነቱ መንስኤ በአገር ውስጥ በቂ ምርት ባለመኖሩ የተፈጠረ ነው ሲሉ ገልጠዋል።
በአገር ውስጥ በቂ ምርት አለመመረቱ በገሀድ እየታየ ኢኮኖሚው 11 በመቶ አደገ ብሎ ለመናገር መሞከር አስጋሪ መሆኑንና ኢህአዴግ እስከ ዛሬ ሲያቀርበው የነበረው ፐሮፓጋንዳ መልሶ እየመታው መሆኑን ገልጧል። ህዝቡ ” ኢኮኖሚው ካደገ ለምን ዋጋ ይጨምራል፣ ዋጋ እንኳ ቢጨምር የሰዎች የገቢ መጠን ለምን አልጨመረም? በማለት መጠየቅ መጀመሩ የአቶ መለስ የ11 በመቶ ፕሮፓጋንዳ ውጤት አልባ እየሆነ መምጣቱን እንደሚያሳይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው እውነታና ኢህአዴግ የሚያስወራው ፐሮፓጋንዳ ህዝቡ ኑሮአችን መሻሻሉን የምናየው በጓዳችን ሳይሆን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው እንደሚል አስታውሰዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ 99 ነጥብ ዘጠኝ የሚሆኑ መምህራን በተደረገላቸው የእርከን ጭማሪ መርካታቸውን፣ ጥቂት ከ500 የማይበልጡ መምህራን ጭማሪውን የተቃወሙት አንድም ጭማሪው የእርከን ጭማሪ መሆኑን ሳያውቁ የደሞዝ ጭማሪ ስለመሰላቸው፣ ሌላም በአስተማሪነት ያልተዋጣላቸው የአስተማሪነት ችግር ያለባቸው ምግባረ ብልሹዎች አጋጣሚውን ተጠቅመው ችግራቸውን ለመሸፋፋን መሞከራቸው እንዲሁም አንዳንዶች ከሻእቢያ፣ ግንቦት 7 እና ኦነግ የተሰጣቸውን የማተራመስ እና ብጥብጥ የማስነሳት ስትራቴጄ ተግባራዊ ለማድረግ ነው ብለዋል። አቶ መለስ የተወሰኑ መምህራን በአማራ እና በአዲስ አበባ መባረራቸው እንዳላሳዘናቸው ይልቁንም ቀደም ብለው መባባረር እንደነበረባቸው ገልጠዋል፣ የአመጽ ሀይሎች መምህራን ተቃውሞአቸውን ወደ አመጽ እንዲቀይሩ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል።
የአቶ መለስ ንግግር መምህራንን ማሳዘኑን ኢሳት የነጋጋራቸው መምህራን ገልጠዋል። በምእራብ ጎጃም በዳንግላ ወረዳ የሚያስተምሩት መምህር ሰው አገኝ አለሙ በተደረገው የደሞዝ ጭማሪ እንኳን የኢህአዴግ አባል ያልሆኑት ቀርቶ አባል የሆኑትም ማዘናቸውን ገልጠዋል::
መምህር ሰዋ አገኝ እንዳሉት አገዛዙ ወደ ለየለት አምባገነንነት በመግባቱ በመምህራን እና በአገዛዙ መካከል ያለው ቅራኔ የሚታረቅ አይደለም::
አቶ መለስ በንግግራቸው በደቡብ ክልል ስለተፋነቀሉት የአማራ ተወላጆች እና ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ እንቅስቃሴም ገለጣ ሰጥተዋል። የተለያዩ አስተያየቶችን አሰባስበን በነገው ዘገባ እናቀርባለን።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide