ማተሚያ ቤቶች ሳንሱር ማካሄድ ጀመሩ፣ የህትመት ስራ አደጋ ውስጥ ወድቋል ተባለ

ሚያዚያ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በስልጣን ላይ ያለው መንግስት አስከብረዋለሁ የሚለው ህገ መንግስት በአንቀጽ 29 ላይ ማንኛውም ሳንሱር ወይም ከህትመት በፊት የሚደረግ የጽሁፍ ይዘት ቁጥጥር እንደማይኖር ቢደነግግም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በህትመት ስራ አንጋፋ የሆነው ብርሀን እና ሰላም ሳንሱር መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

ድርጅቱ የህትመት ስራ ስታንዳርድ ውል በሚል ርእስ ያወጣው አዲስ የስራ ውል በአንቀጽ 10 ላይ ህግን የተላለፈ ይዘትን አለማተም በሚል ርእስ ስር ባሰፈረው ጽሁፍ ” አታሚው በአሳታሚው እንዲታተም የቀረበለት የጽሁፍ ስክሪፕት ህግን የሚተላለፍ ስለመሆኑ ለማመን በቂ ምክንያት ካለው አላትምም የማለት መብት አለው።” በማለት በይፋ ሳንሱር መጀመሩን አስታውቋል።

ድርጅቱ አንድ ጋዜጣ ህግን መተላላፉን እና አለመተላለፉን የሚያውቅበት መንገድ እንዳለውም በአንቀጽ 10 ተራ ቁጥር 10 ነጥብ 2 ላይ”  አታሚው አሳታሚው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህትመት ይዘት የማውታት ዝንባሌ ያለው መሆኑን ለማመን በቂ ምክንያት ካለው በማናቸውም ጊዜ ውሉን ለማቋረጥ ወይም ለመሰረዝ ይችላል።” ሲል አስፍሯል። ይህ አዲስ አዋጅ የፍርድ ቤቶችን ስልጣን የቀማ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህገመንግስቱንም የሚጥስ ነው።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ጠበቃ መንግስት ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያቆመው መወሰኑን ገልጠው፣ አዲሱ ድንጋጌ የተወሰኑ ጋዜጠኞችን ለማስቆም ተብሎ የወታ መሆኑን ገልጠዋል። ለመሆኑ ማታሚያ ቤቱ የአንድን ጋዜጣ ዘንባሌ እንዴት ሊያውቅ ይችላል፣ ህግን መተላላፍና አለመተላለፍን የ አየው ፍርድ ቤት እንጅ አታሚ ድርጅት ምን አገባው ሲሉ ውሳኔው ከበላይ አካል የመጣ መሆኑን ገልጠዋል። አቶ መለስ አንድን ጋዜጣ ለመዝጋት ቆርጠው ተነስተዋል፣ ያም ጋዜጣ ፍትህ ጋዜጣ ነው፤ አቶ መለስ በኢትዮጵያ ውስጥ ከራሳቸው ድምጽ ውጭ ምንም አይነት ሌላ ደምጽ መስማት አይፈልጉም በማለት ውሳኔው ከጭንቀት የመነጨ መሆኑን ገልጠዋል።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ጋዜጦች የሚታተሙት በብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት  ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ብቸኛውን ጠንካራ ነጻ ጋዜጣ የሆኑውን ፍትህን ለመዝጋት በመለስ መንግስት በኩል የተጀመረው ዘመቻ እንደቀጠለ ነው።  የመንግስት እና የገዢው ፓርቲ ልሳናት በፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች ላይ የስድብ ውርጅብኝ ማቅረባቸውን  በቀጠሉበት በአሁኑ ጊዜ፣  የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መጥሪያ ደርሶአቸዋል።  ሚያዚያ 4 ቀን 2004 ዓም ለፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያሳየው ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሚያዚያ 11 ቀን 2004 ዓም ከጧቱ 3 ሰአት ከ30 ደቂቃ ላይ ችሎት ተገኝቶ በቀረበበት ክስ ዙሪያ አስተያየቱን እንዲያቀርብ ተጠይቋል።

አቃቢ ህግ በፍትህ ጋዜጣ ላይ ያቀረበው ክስ  የአቶ አንዱአለም አራጌን የቃልቲ ደብዳቤ ማተም፣ መጋቢት 21 በወጣው ጋዜጣ ላይ ክሱን የሚያጣጥል ዘገባ ማቅረብ፣ አቃቢ ህግ የሌለ ማስረጃ ለማቅረብ መሞከሩን የሚጠቅስ ዘገባ መስራት የሚሉት ይገኙበታል። ውድ ተመልካቾቻችን የብርሀን እና ሰላምን አዲስ ውል በድረገጻችን ላይ ማንበብ ይችላሉ።

__________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide