ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ለቱርክ ተላልፈው እንደሚሰጡ ቃል የገባችውና በቱርክ መንግስት ጥያቄ ቀርቦባቸው የነበሩ የነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች ለጀርመን ባለሃብቶች በሽያጭ ተዘዋወሩ።
ቱርክ ትምህርት ቤቶቹ አሸባሪ ድርጅት ብላ ከፈረጀችው ከጉለን ንቅናቄ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያለው ነው በማለት ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶቹን አስተላልፋ እንድትሰጣት በይፋ ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።
በቅርቡ በቱርክ ጉብኝትን ያደረጉት የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ መንግስት ጥያቄ የተነሳባቸውን ትምህርት ቤቶች አስተላልፎ እንደሚሰጥ ቃል ገብተው እንደነበር የቱርኩ የዜና አገልግሎት አናዱሉ ዘግቧል።
ይሁንና ትምህርት ቤቶቹ የሚያስተዳድሩ የቱርክ ባለሃብቶች ትምህርት ቤቶቹ ለጀርመን ባለሃብቶች በሽያጭ እንደተዘዋወሩ ማረጋገጣቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ አስነብቧል።
የነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጉዳይ አስተባባሪ የሆኑት ከሊል አይዲን ሽያጩ የተከናወነው ትምህርት ቤቱ በነበረው እቅድ መሰረት ነው ብለዋል።
የጀርመንን የቢዝነስና የትምህርት ስርዓት በኢትዮጵያ ለማስፋፋት የወሰደነው ዕርምጃ ነው የሚሉት ሃላፊው ምንም አይነት የመንግስት ተፅዕኖ ወይም ጥያቄ እንዳልቀረበላቸው አስረድተዋል።
የኢትዮ-ተርኪሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ፣ መቀሌና አለምገና ከተሞች አምስት ትምህርት ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ2004 አም መመስረቱንም ከተቋሙ ድረገጽ ለመረዳት ተችሏል። ፕሬዚደንት ሙላቱ በቱርክ ጉብኝታቸው ትምህርት ቤቶቹን ለመስጠት ቃል ስለመግባታቸው ተጠይቀው የነበሩት ከሊል አይዲን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው እንደነበርም ይታወሳል።
የትምህርት ቤቱ ሃላፊ ጥያቄን አስነስቶ የሚገኘው የነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ ትምህርት ቤቶች በምን ያህል ገንዘብ እንደተሸጠና የባለሃብቶቹን ማንነት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
መንግስት ለቱርክ አስተላልፎ ቃል ስለገባቸው ትምህርት ቤቶች ሽያጭ በተመለከተ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም። የቱርክ መንግስት ባለፈው አመት በሃገሪቱ ተሞክሯል ያለው የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ በጉለን ንቅናቄ የተቀነባበረ ነው ሲል ድርጁትን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።
የቱርክ ባለስልጣናት በዚህ በአሜሪካ የሚገኙት የንቅናቄው መስራችና ሃላፊ ፋቱላህ ጉለን ተላልፈው እንዲሰጧቸው ጥያቄን ቢያቀርቡም ለሃላፊው ጥገኝነትን ሰጥታ የምትገኘው አሜሪካ ጥያቄን ሳትቀበለው ቀርታለች።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው ሃገሪቱ የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ ያለችውን ድርጊት ምክንያት በማድረግ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የጅምላ እስራት በመፈጸም ላይ መሆኗን ይገልጻሉ።