በሶማሌ ክልል የኮሌራ በሽታ በመዛመት ላይ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ በበርካታ ዞኖች የኮሌራ በሽታ በመዛመት ላይ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ይፋ አደረገ።

ቢርቆድ፣ ቀብሪደሃር፣ ደገሃቡር፣ ሽኮሽና፣ እና ጉናጉዱ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች እየተዛመተ ባለው በዚሁ ተላላፊ በሽታ እስካሁን ድረስ በትንሹ 103 ሰዎች መያዛቸውን የሶማሌ ክልል የጤና ባለሙያዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ለሁለተኛ ጊዜ በክልሉ ተከስቶ የሚገኘው የድርቅ አደጋ ከፍተኛ የውሃ እጥረት እንዲከሰት በማድረጉ ሳቢያ ውሃ ወለድ በሽታዎች በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች ተጨማሪ ስጋት ማሳደሩ ተነግሯል።

የኮሌራ በሽታው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ይዛመታል የሚል ስጋት በመኖሩም ስምንት ሃኪሞችና 150 የጤና ባለሙያዎችን ያቀፈ 14 የጤና ቡድን ወደ ስፍራው እንዲያቀና መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃሰን እስማዔል ዋቢ በማድረግ የመንግስት ተቋማት ዘግበዋል።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሌ ክልል እየተባባሰ የመጣው የድርቅ አደጋ አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገለት በሰው ህይወት ላይ አደጋን  ሊያስከትል እንደሚችል ማሳሰቡ ይታወሳል።

በአራት ክልሎች በአዲስ መልክ ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ይኸው የድርቅ አደጋ በተለይ በሶማሌ ክልል በሚገኙ አብዛኞቹ ዞኖች አስከፊ የሆነ የምግብ እጥረት እንዲከሰት ያደረገ ሲሆን፣ ከምግብ እጥረቱ በተጨማሪ ኮሌራ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ለነዋሪው የጤና ስጋት መሆናቸውም ታውቋል።

በሶማሌ ክልል አስከፊ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸው ያሉ ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ ሰዎች ለእርዳታ አቅርቦት አመቺ እንዲሆን ተብሎ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን፣ የኮሌራ በሽታው በቶሎ የመዛመት እድል እንደሚኖረው የጤና ባለሙያዎች አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በክልሉ ያለው የድርቅ አደጋ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ባለፈው ሳምንት ከመጠባበቂያ በጀቱ 18.5 ሚሊዮን ዶላር ልገሳ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ድርጅቱ የሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ተከትሎ መንግስት ከመጠባበቂያ ክምችት አስቸኳይ ምግብ ለተጎጂዎች እንዲከፋፈል የወሰነ ሲሆን፣ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው አቅርቦቱ መዘግየት ማሳየቱን ይገልጻሉ።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የድርቁ አደጋ የተሰጋውን ጉዳት እንዳያስከትል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ እና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው አዲስ የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ተጋልጠው ይገኛሉ።

መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የድርቁን አደጋ ለመከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ በቅርቡ ይፋ አድርገዋል።

ከዚሁ ከድርቅ አደጋ ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሶማሊላንድ ግዛት በድርቅ ለተጎዱ ሰዎች 8ሺ ኩንታል እህልና ከ26ሺ ካርቶን በላይ ብስኩትና ወተት መለገሷን አስታውቃለች።

ራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ባወጀችው ሶማሊላንድ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለምግብ ድጋፍ ተጋልጠው እንደሚገኙ ተመልክቷል።