(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2010) በኢትዮጵያ በነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ላይ የተጀመረው የዕቀባ ዘመቻ ውጤታም በሆነ መንገድ መቀጠሉ ተገለጸ።
መንግስት ደግሞ በጉዳዩ ላይ ተከታታይ መግለጫዎችን በመስጠት ስራ ላይ መጠመዱ ታውቋል።
የዕቀባ ጥሪውን ይፋ ያደረገው ቄሮ ደግሞ ተጨማሪ ርምጃዎችን እንደሚቀጥል ዛሬ አስታውቋል።
ማክሰኞ የተጀመረውን የነዳጅ ተአቅቦ ጥሪ ተከትሎ የነዳጅ ቦቴ ባለንብረቶች ከኢንሹራንስ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲያነሱ፣ሾፌሮቹ ደግሞ የደህንነት ዋስትና በማቅረብ ለመጓዝ ፍቃደኛ አለመሆናቸው ታውቋል።
በመንግስት በኩል ኮማንድ ፖስቱ ያጅባችኋል፣እንዲሁም የኢንሹራንስ ጥያቄ ጨርሶ ሊያሳስባችሁ አይገባም በሚል ለማግባባት እና ለማስገደድ ተሞክሯል።
ሆኖም በሾፌሮች እና በባለንረቶቹ አካባቢ ያለውን ስጋት መቅረፍ ባለመቻሉ የነዳጅ ዕጥረቱ መቀጠሉ ታውቋል።
መንግስት ለማረጋጋት ከበቂ በላያ ነዳጀ በመግባት ላይ መሆኑን በመናገር ላይ ይገኛል።
ከበቂ በላይ ነዳጅ እየገባ መሆኑ እየተገለጸ ባለበት በአዲስ አበባ ከተማ ጭምር በነዳጅ ማደያዎች ላይ ስለሚታየው ወረፋ እንዲሁም በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ላይ ነዳጅ መጥፋቱን በተመለከተ የመንግስት ባለስልጣናት የሰጡት መግለጫ የለም።
የነዳጅ ቦቴ ባለንብረቶች ለመንቀሳቀስ መስጋታቸውን ተከትሎ ነዳጅ በበርሜል እየተጫነ በፒክ አፕ እና መሰል ተሽከርካሪዎች በመጓጓዝ ላይ መሆኑንም መረዳት ተችሏል።
ነዳጅ ያልጫኑ ባዶ ቦቴዎች በአዲስ አበባ ከተማ ወስጥ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግም የማረጋጋት ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ የሆነውን የነዳጅ ቦቴዎች የዕቀባ ርምጃ ለማጠናከር እና ተጽዕኖው ይበልጥ ጉልህ እንዲሆን በሚል ቄሮ ዛሬ ባወጣው ማሳሰቢያ የሚከተሉት ቀጣይ ርምጃዎች እንደሚኖሩ አመልክቷል።
“የነዳጅ ተአቅቦው አዲስ አበባ ውስጥ ባሉት የነዳጅ ማደያዎች ላይ ፍፁምና የተሟላ ተፅዕኖ እንዲኖረው፥ አስፈላጊ የሆኑ ተከታታይ ርምጃዎች ይወሰዳሉ።
- ሁኔታው እየታየ እንዳስፈላጊነቱ የተአቅቦው ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ይደረጋል።
- እስካሁን አትኩሮት የተደረገው ዕቀባ የቦቴ ተሽከርካሪዎች ላይ ቢሆንም ወያኔ ሌላ አማራጭ ልትጠቀም ትችላለች ከሚል እሳቤ በመነሳት የነዳጅ ተአቅቦው ከሰበታ ተነስቶ ጂቡቲ እስከሚገባ ድረስ ያለውን የባቡር መስመር ለማስቆም የሚችል እንዲሆን እንደአስፈላጊነቱ ርምጃ ይወሰዳል። የባቡር መስመሩ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ስለሆነ ይኸን ማድረግ አያስቸግርም”በማለት በቀጣይ ስለሚኖሩ ርምጃዎች ማሳሳቢያ ያወጣውና የተአቅቦ እንቅስቃሴውን የሚያስተባብረው የቄሮ ቡድን ሁሉም ወገን ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ ጥሪውን አስተላልፏል።