ጠንካራ መግለጫ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ታዬ ደንደዓ ታሰሩ

ጠንካራ መግለጫ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ታዬ ደንደዓ ታሰሩ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) በሞያሌ የደረሰውን ጭፍጨፋ ሆን ተብሎ የታቀደ እንጅ በስህተት የተፈጸመ ነው ብለው ለማመን እንደሚቸገሩ የገለጹት የኦሮምያ ፍትህ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደዓ በወታደራዊ እዙ ትዕዛዝ እንዲታሰሩ ተደርጓል። አቶ ታዬ ለአሜሪካ እና ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ መግለጫዎችን ከሰጡ በሁዋላ ብዙዎች እንደሚታሰሩ ግምታቸውን ሰጥተው ነበር።
አቶ ታዬ ወደ ስራ በሚያመሩት ወቅት በወታደሮች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ባለቤታቸው ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ የታሰሩት አቶ ታዬ፣ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለመመረቅ ሳምንት ሲቀራቸው ታስረው ነበር።
ሰሜን ሸዋ ኩዩ ከተማ ተወልደው ያደጉት አቶ ታዬ በ1996 ዓም ለ3 ዓመታት ታስረው በመጨረሻም ፍርድ ቤት ነጻ ብሎአቸዋል። ከዚያም የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ለመጨረሽ ወደ ዩኒቨርስቲ ከገቡ በሁዋላ፣ እንደገና ሊመረቁ አራት ቀናት ሲቀራቸው በ2001ዓም የኦነግ ደጋፊ ተብለው ታስረዋል። ለ10 ዓመታት በእስር ቤት ያሳለፉት አቶ ታዬ፣ በቆይታቸውም በኦሮምኛ “ገላ ደሎታ” ወይም “ለመጪው ትውልድ ስንቅ” የሚል ተረትና ምሳሌ መጽሃፍ አዘጋጅተዋል። አቶ ታዬ በ2008 ዓም ከእስር ሲፈታ፣ ከ16 ዓመታት በፊት የጀመረውን ትምህርት ያጠናቀቀ ሲሆን፣ የኦሮምያ ክልል የፍትህ ቢሮ ሃላፊ ሆኖ በሚሰሩበት ወቅት የተለያዩ ጥናቶችን እያጠኑ እንደነበር በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር ባዳረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።
በአቶ ታዬ ላይ የተወሰደው እርምጃ በክልሉ ውስጥ በድፍረት ሃሳባቸውን እየገለጹ ያሉትን የኦህዴድ ባለስልጣናት ለማሸማቀቅ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል አንዳንዶች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።