የትግራይ ክልል የአማራ ክልል ይቅርታ እንዲጠይቅ አሳሰበ
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ/ም ) የትግራይ ክልል መንግስት፣ የአማራ ክልል መንግስት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓም በወልቃይትና በራያ የማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ የሚቃወም መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በመግለጫውም “የትግራይ ክልል ከመግለጫው በተቃራኒ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ተወላጆች ሕገ መንግስታዊ መብታቸውና ነፃነታቸው ተከብሮ በሰላምና በክብር የሚኖሩባት ክልል ሆና እያለች ዜጎች በማንነታቸው የሚፈናቀሉባትና በአማራ ክልል ሰላም ችግር ፈጣሪ መባሏ አሳዛኝና ከትንኮሳ የማይተናነስ ጠባጫሪ አቋም ነው።” ብሎአል።
የትግራይ ክልል በመግለጫው፣ የአማራ ክልል ሕገ መንግስቱ በማንነት ጉዳይ ላይ ያስቀመጠውን ስርዓት በመጣስ በሌላ ክልል የውስጥ ጉዳይ ጠልቃ መግባቱ የሚያረጋግጥ ነው ብሎአል። በራያም ሆነ በወልቃይት አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮችም የአማራ ክልል መንግስት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል ሲል ተጠያቂነቱን ወደ አማራ ክልል አሸጋግሮታል።
የትግራይ ክልል በማጠቃለያው “ የአማራ ክልል መንግስት ያወጣው መግለጫ መሰረታዊ የሆነ ሕገ መንግስታዊ ጥሰት ያለበትና በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረው አብሮነት የሚጎዳ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲታረም እና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ለትግራይ ህዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ በጥብቅ እናሳስባለን።” ብሎአል።
የአማራ ክልል ለትግራይ ክልል መግለጫ የሰጠው መልስ የለም። የፌደራሉ መንግስትም በዚህ ጉዳይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።