በራያ ቆቦና ዋጃ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 14/2011) በራያ ቆቦና ዋጃ ተቃውሞ መቀስቀሱ ተሰማ።

ህዝቡ መንገድ በመዝጋት የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ መግታቱን የደረሰን ዜና ያመለክታል።

በራያ አላማጣ አፈናውና አፈሳው ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ መሆኑንም ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጸዋል።

ባለፉት አራት ቀናት ከአላማጣ፣ ከዋጃ ከጡሙጋና ከቆቦ ራያ የታፈሱ ወጣቶች ወደየት እንደተወሰዱ እንደማያውቁ ቤተሰብ በስጋት በመግለጽ ላይ ነው።

ከአላማጣ ከ10 በላይ የሀገር ሽማግሌዎችና የከተማዋ ታዋቂ ግለሰቦችም መታሰራቸው ታውቋል።

በአዲስ አበባ ለዛሬ ተጠርቶ የነበረው የራያ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ መከልከሉን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

እንደአዲስ የተቀሰቀሰው የራያው ውጥረት በአራተኛ ቀኑ ራያ ቆቦ፣ ዋጃና ሌሎች አከባቢዎች ደርሷል።

በመሆኒም የህዝብ ቁጣ መቀስቀሱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በመሆኒ እየተካሄደ ባለው ተቃውሞ የትግራይ ልዩ ሃይል ርምጃ በመውሰድ ላይ ሲሆን ከመቀሌ ተጨማሪ ሰራዊት ወደ መሆኒ በመጓዝ ላይ መሆኑም ታውቋል።

በራያ ዋጃ እና በራያ ቆቦ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ምክንያት በዚህ ሰዓት መንገድ መዘጋቱም ተመልክቷል።

በዚህም ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ የሚሄድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ የታገተ ሲሆን ከራያ አላማጣ ታፍነው የተወሰዱት ወገኖች ካልተለቀቁ የታገተውን አውቶብስ እንደማይለቁ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ልዩ ሃይል ከራያ አላማጣ ታፍነው የተወሰዱ ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶች እና ባለ ሃብቶች ቁጥር ከ200 በላይ የደረሰ ሲሆን 90 የሚሆኑት በማይጨው እስር ቤት እንደታሰሩ ለማወቅ ተችሏል።

ቀሪዎቹን ወዴት እንደወሰዷቸው አይታወቅም ነው የተባለው።

ከየቦታው እየታፈሱ የሚወሰዱ ሰዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ቁጥራቸውን በትክክል ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ትላንት ሌሊቱን አፈናና አፈሳው በስፋት መካሄዱን የሚጠቅሱት ነዋሪዎች የትግራይ ልዩ ሃይል ወዴት እየወሰዳቸው እንዳለ ባለመታወቁ ቤተሰብ ስጋት ውስጥ መሆኑን ይገልጻሉ።

ዛሬ አላማጣ ጸጥ ረጭ ብላ የዋለች ሲሆን ማንኛውም እንቅስቃሴ ተገቶ የትግራይ ልዩ ሃይል ሰራዊት ፈሶባት እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ህዝቡና የትግራይ ሃይል ተፋጦ ያለባት አላማጣ ነዋሪ ታፍነው የተወሰዱ ሰዎች በአስቸኳይ ካልተለቀቁ የተጠናከረ ተቃውሞ እንደሚያደርግ እያስጠነቀቀ ነው ተብሏል።

በሌላ በኩል ህዝቡ ላነሳው የማንነት ጥያቄ ድጋፍ ሰጥታችኋል የተባሉ የራያ ሚሊሻዎችን የትግራይ ክልል መንግስት ትጥቅ ሊያስፈታቸው እየሞከረ መሆኑን የኢሳት የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።

የማንነት ጥያቄ ይደግፋሉ ፣ ከህዝብም ጎን ቆመዋል የተባሉ የራያ ሚሊሺያዎችን የመለየት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑም ታውቋል።

ከዚህ ሌላ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች የራያን የመብት ጥያቄ ለመንግስትና ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሳወቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን ለማጥቃት በህወሃት በኩል መታቀዱን የሚገልጽ መረጃ ለኢሳት ደርሶታል።

በተለይ በአዲስ አበባ ያሉትን የኮሚቴውን አባላት ለማፈን ገንዘብ መመደቡን ነው ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የራያ መብት ይከበር በሚል በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ መሰረዙ ተገልጿል።

ሰልፉን ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ ለአዘጋጆቹ የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ የተደራጁ ሃይሎች ሰልፉን ተገን አድርገው አደጋ ሊያደርሱ መሆኑን ደርሼበታለሁ የሚል ምክንያት መስጠቱን ኢሳት ከአዘጋጁ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።