የትምባሆ ፍላጎት መቀነስና የአቅርቦት ቁጥጥር ሥርዓት አገራት እንዲዘረጉ የሚያስገድደውን ዓለምአቀፉ የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ረቂቅ አዋጅ በፓርላማ ሊጸድቅ ነው፡፡

፲፬( አስራ አራት )ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :- ፓርላማው እ.ኤ.አ በ2003 በጄኔቭ የወጣው ኣለምአቀፍ የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ኢትዮጽያ ፈራሚ አገር የነበረች ሲሆን ይህንን ለማጽደቅ ረቂቅ ሕግ በዛሬው ዕለት ለፓርላማው ቀርቦለት በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በሃላ ለሚመለከተው ኮሚቴ መርቶታል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ላይ በኢትዮጽያ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል 8በመቶ ያህሉ የትምባሆ ምርቶችን እንደሚጠቀሙ ጥናቶችን ጠቅሶ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ወደ 41 በመቶ ያህል ወጣቶች ደግሞ ትምባሆ በሚጨስበት አካባቢ ውስጥ የሚያዘውትሩ በመሆናቸው ለጤና ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን ይጠቁማል፡፡ ይህ ኮንቬንሽን ኢትዮጽያ መቀበልዋ በተለይ ከትምባሆ ጋር በቀጥታ የተያያዙ የጤናና ማህበራዊ ቀውሶችን ለመታደግ ያስችላል ተብሎአል፡፡

ኮንቬሽኑ የትምባሆ ቁጥጥር ስትራቴጂዎች በዋንኛነት የትምባሆ ፍላጎትን እና አቅርቦትን ላይ ያነጣጠሩ እንዲሆኑ ያስገድዳል፡፡ በኮንቬሽኑ ክፍል ሶስት ደግሞ የተለየ የፍላጎት መቀነሻ ዘዴዎች ማለትም የዋጋና የግብር እንዲሁም ዋጋ ነክ ያልሆኑ የትምባሆ መቀነሻ ስልቶች እንዲተገበሩ ያዛል፡፡

ይህ ኮንቬንሽን በተለይ ሲጋራና የሲጋራ ውጤቶችን በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች፣በምግብ ቤቶች፣በት/ቤቶችና በመመሳሰሉት ስፍራዎች መጠቀም ስለሚከለክል ኢትዮጽያም ይህን ተግባራዊ እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡