ታኅሣሥ ፭ (አምስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በሚካሄደው የመማር ማስተማር ሂደት የትምህርት ጥራቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀ መምጣቱን ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡
በክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች በሚካሄዱ የመምህራን ቅጥር ከአስረኛ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል መሸጋገር ያልቻሉ ተማሪዎችን ያካተተ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ የሚቀጠሩት ረዳት መምህራን ምንም ዓይነት ስልጠና ሳይሰጣቸው ወደ ሙያው ገብተው እንዲሰሩ በመደረጋቸው በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ ከፍተኛ የጥራት ማሽቆልቆል እየታየ ነው፡፡
ወረዳዎች በዚህ ዓይነት መምህራን መቅጠር ከጀመሩ ረዥም ዓመታት በማስቆጠራቸውና በየደረጃው ያሉ የገዥው መንግስት አመራሮች ረዳት መምህራኑ ተገቢ የሆነ ስልጠና እንዲያገኙ ባለማድረጋቸው በ2008/2009 ዓም. በአስረኛ ክፍል ላይ የሚታየው የውጤት ማሽቆልቆል የዚህ ስራ ውጤት መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ባለፈው ዓመት በአንድ ወረዳ ብቻ የ10ኛ ክፍል ሀገር ዓቀፍ ፈተናን ከተፈተኑ 423 ተማሪዎች ውስጥ 354 ተማሪዎች ፈተናውን ማለፍ አለመቻላቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ባለሙያዎች በማስረጃነት ይጠቅሳሉ፡፡
በተያያዘ ዜና በክልሉ የሚካሄደው የጎልማሶች ትምህርት ስኬት አደጋ ላይ መሆኑን ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ የጎልማሶች ትምህርት እንዲከናዎን የተቀየሰው በሶስት ቢሮዎች ቅንጅት እንዲሰራ ታስቦ እንደሆነ የሚናገሩት ለረዥም ጊዜ በትምህርት ስራ ላይ የቆዩ ባለሙያዎች የግብርና፣ ጤናና ትምህርት ቢሮዎች ቅንጅታዊ አሰራር ወደ “ዜሮ” እየወረደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየጊዜው በሚደረጉት የትምህርት ስብሰባዎች የጎልማሶችን ትምህርት በተመለከተ የሚቀርቡ ሪፖርቶች በሙሉ የሃሰት መሆናቸውን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ጉዳዩን በየትምህርት ቤቱ ተከታትለው በሚያዩበት ጊዜ አብዛኛው ጎልማሶች በትምህርት ገበታ ላይ እንዳልሆኑ ሊያረጋግጡ እንደቻሉ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡
በጎልማሶች ትምህርት ዙሪያ የተለያዩ መጽሐፍት ቢዘጋጁም በተግባር ሲታይ ግን ከትምህርት ባለሙያዎች ውጭ የትኛውም ቢሮ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ ዘርፉን ለማጠናከር የሚያደርገው እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ትምህርቱ በአግባቡ እየተካሄደ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል፡፡