(ኢሳት ዜና–ሕዳር 8/2010) የትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተከሰቱ ሁኔታዎችን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ችግሮቹን እንዳባባሰ ተገለጸ።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የችግሮቹ ዋነኛ ምንጭ ትንሽ የሚባሉ ተማሪዎች ናቸው ሲል የሰጠው ሰበባዊ መግለጫ ለችግሩ መባባስ በምክንያትነት ተቀምጧል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ያጋጠሙ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ በተቋማቱ የተፈጠረው ችግር በ20ና 30 ተማሪዎች ማሳበባቸው ችግሩን እንዳባባሰው ነው ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የገለጹት።
በከፍተኝ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈጣሪዎቹ ከ20ና 30 የማይበልጡ ተማሪዎች ከሆኑ እንዴት ችግሩን መፍታት ያቅተዋል በማለት ተማሪዎቹ ጠይቀዋል።
የተማሪን ጥያቄ በማድበስበስና በማሳነስ የመጣ ለውጥ ባለመኖሩ የትምህርት ሚኒስትሩ በይፋ ይቅርታ ጠይቀው ለተማሪው ጥያቄ ምላሽ ቢሰጡ ይሻላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌጤ ለመንግስትና የፓርቲ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል የሚማሩ ተማሪዎችን የማዟዟር ውሳኔ የወሰነው የትምህርት ሚኒስቴር እንደሆነ ገልጸዋል።
የውሳኔው መነሻም በሁለቱ ክልሎች ጥቂት የጥገኛ ሃይሎች በፈጠሩት ችግር ምክንያት መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን የምደባ ቅያሬ አስመልክቶ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን መመሪያ እንደማያምኑበት በግልጽ ማስቀመጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የሁለቱን ክልል ሕዝብ በጠላትነት እንዲፈራረጅ የሚያደርግና የፌደራሊዝም ስርአቱን የሚያበላሽ እንደሆነም ተናግረው ነበር።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም ቢሆን እንዲህ አይነቱን አሰራር የሚያምንበት አይመስለኝም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በትምህርት ሚኒስቴር መመሪያ ላይም ሆነ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት በሰጡት አስተያየት ላይ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።