በባህር ዳር የቦምብ ጥቃት ተፈጸመ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 8/2010)ከባህርዳር ከነማ ጋር ውድድሩን ሊያካሂድ ባህርዳር የገባው የአክሱም ከነማ እግር ኳስ ቡድን ያረፈበት ሆቴል ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ውጥረት መንገሱ ተሰማ።

ማምሻውን የልዩ ሀይል ፖሊሶች ተጫዋቾቹን ከሆቴሉ ለማስወጣት እየሞከሩ መሆናቸው ታውቋል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ነገ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቀው ጨዋታ ግን የተባለ ነገር የለም።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ /ባቱ/ ከተማ በግለሰቦች መካከል ተቀስቅሷል የተባለ ጸብ ወደ ሌሎች ተሸጋግሮ ከ10 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞትና ለበርካቶች መቁሰል ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

በመቱ ዩንቨርስቲ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሙሉ በሙሉ መስተጓጎሉ ተሰምቷል።

የአክሱም ከነማ ቡድን ባህር ዳር ሲገባ ያወቀም ሆነ በግልጽ የተነገረ ነገር አልነበረም።

ነገር ግን ቡዳኑ ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ ንብረትነቱ የህወሃት የደህነነት ሰው እንደሆነ በሚታወቀውና ቀበሌ 02 በሚገኘው ዳግማዊ ዮሃንስ ጋርደን ሆቴል ማረፉ የታወቀው በሆቴሉ ላይ የቦምብ ፍንዳታ ከተከሰተ በኋላ ነው።

በተፈጸመው ጥቃትም እስካሁን ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውናን ወደሆስፒታል መወሰዳቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ማምሻውን የልዩ ሀይል ፖሊሶች ተጫዋቾቹን ለማስወጣት እየሞከሩ መሆኑን ከመረጃው ለማወቅ ተችሏል።

እስካሁን ጥቃቱን ማን ፈጸመው ለሚለው ግን ምላሽ አለተገኘለትም።

ከተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ጋር ተያይዞ ነገ ይካሄዳል የተባለው ጨዋታ በመርሃ ግብሩ መሰረት ይካሄድ አይካሄድ የታወቀ ነገር የለም።

የከተማው ህዝብ ጨዋታውን ለመመልከት ወደስፈራው የመሄዱ ጉዳይም አጠራጣሪ ሆኗል።

እንደ ኢሳት ምንጮች ከሆን ከቦምብ ጥቃቱ ጋር ተያይዞ በከተማዋ ውጥረት ነግሷል።

ከባህርዳር ከነማ ጋር የአክሱም ከነማ እግር ኳስ ቡድን ጨዋታውን በባህርዳር ብሔራዊ ስታዲየም እንዲያካሂድ መርሃ ግብር ወጥቶለታል።

ነገር ግን ከዚህ በፊት በከተማዋ ይካሄዱ የነበሩ የሊግ ጨዋታዎች ሲካሄዱ የነበሩት በአጠቃላይ በባህርዳር ዩንቨርስቲ ፔዳ ሜዳ ሲሆን አሁን ይህ ጨዋታ በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየሙ እንዲካሄድ መወሰኑ ጥያቄ አስነስቷል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል ዝዋይ /ባቱ/ ከተማ በግለሰቦች መካከል ተቀስቅሷል የተባለ ጸብ ወደ ሌሎች ተሸጋግሮ ከ10 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞትና ለበርካቶች መቁሰል ብሎም መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

በቡድን የተደራጁ ወጣቶች ወደ ከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ነዋሪዎችን ሲደበድቡና ሲያዋክቡ መዋላቸው ተነግሯዋል።

ችግሩ በተከሰተበት ሰዓት የከተማው ፖሊስ በፍጥነት ባለመድረሱና በቂ ሃይል ይዞ ባለመምጣቱ አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት እንዳልተቻለ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በግጭቱ 11 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የአካባቢው ምንጮች አስታውቀዋል።

በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውና የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በከተማዋ አስተዳደር እርዳታ እየተደረጋላቸው መሆኑ ሲጠቀስ ነዋሪዎቹ አሁንም ስጋት ወስጥ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ በመግለጫቸው እንደጠቀሱት በመቱ ዩንቨርሲቲ ተማሪ የነበሩት የአማራ ተወላጆች ዩኒቨርስቲውን ለቀው በመውጣት በከተማዋ መናሃሪያ ተሰባስበዋል።

እንደቃል አቀባዩ ገለጻ ሌላ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው አካላት ባደረጉት ቅስቀሳ ተማሪዎቹ ከማደሪያቸው ለቀው በመውጣት ለአራት ቀናት በመሰብሰቢያ አዳራሽ አድረዋል።

ችግሩን ለመፍታትና ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በሀይማኖት አባቶች፥ በአባ ገዳዎች፥ በሽማግሌዎች፥ በከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም በዩኒቨርስቲው አካላትና መምህራን ቢለመኑም አሻፍረኝ ማለታቸው ተጠቅሷል።

የክልሉ መንግስት ጸጥታው አስተማማኝ ነው ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ ቢልም ተማሪዎቹ አልተቀበሉትም ።

በተመሳሳይም የደቡብ ተወላጅ ተማሪዎች ዩንቨርስቲውን ለቀው በመውጣት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።