የቴልኮም አዋጅ ነገ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል

ሐምሌ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በነገው ልዩ የፓርላማ ስብሰባ ላይ አወዛጋቢው የቴልኮም አዋጅ እንደሚጸድቅ ለማወቅ ተችሎአል። በአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀር ከፍተኛ ውግዘት የደረሰበት አዲሱ የቴልኮም አዋጅ እንዲጸድቅ የሚደረገው ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግበት ነው።

ስካይፕ እና ሌሎች በኢንተርኔት የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን ማስተናገድ በወንጀል የሚአስከስሰውና እስከ አስር አመትና እስከ 100 ሺ ብር የሚያስቀጣው አዋጅ ከጸደቀ፣ የመለስ መንግስት ማንኛውንም ዘመናዊ የመገናኛ መስመሮችን ሁሉ ለመዝጋት ያለውን ቁርጠኝነት የሚሳይ ነው።

ወጣቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎችን መጠቀም መጀመሩ ያስደነገጠው የመለስ መንግስት እንዲህ አይነቱን እርምጃ የሚወስደው ለአገር ደህንነትና እና ቴሌኮሚኒኬሽንን ከከሲራ ለመታደግ ሲል መሆኑን ይናገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ማነስ፣ ቴሌን የሚቀናቀን ሌላ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ባለመኖሩ መንግስት የሚያቀርበው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ተቀባይነት እንደማይኖረው ተችዎች ይናገራሉ።

አዲሱ የቴሌ ህግ በኢንተርኔት ስልክ መደወል ብቻ ሳይሆን፣ በኢንተርኔት የተደወለን ስልክ የሚቀበለውን ወገንም ወንጀለኛ ያደርጋል። ከአገር ውጭ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሀንና የፖለቲካ ድርጅቶች የስልክ ግንኙነቶችን የሚያደርጉት በቀጥታ መስመር እንዳልሆነ ይታወቃል። መንግስት የደህንነት ስጋት አለብኝ የሚለውም ከዚሁ ፍርሀት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ያክላሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide