ነሃሴ ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ወኪል ከስፍራው ባደረሰን መረጃ አስከሬኑ ዛሬ ንጋት ላይ ተኝቶ ሲታከምበት ከነበረው ከናይሮቢ -ወደ አዲስ አበባ ገብቷል።
እዮብ ከሳምንት በፊት ልጁን በብሽክሊሊት ትምህርት ቤት አድርሶ ከተመለሰ በሁዋላ ቤቱ መግቢያ በር ላይ ሲደርስ ድንገት ሰውነቱ አልታዘዝ ብሎት መዝለፍለፉን የገለጸችው ባለቤቱ ቲና፤ከዚያ እንደምንም የበሩን ደወል ተጭኖ መጥሪያ ካሰማ በሁዋላ መቆም አቅቶት በተደገፈው በር ሸርተት እያለ ወደ መሬት ሲወርድ ደርሰውበት መደንገጣቸውንና በአስቸኳይ በቅርብ ወደሚገኘው ሀያት ሆስፒታል እንደወሰዱት ተናግራለች።
የሀያት ሆስፒአል ሐኪሞች እዮብን ለመርዳት የተሻለ ህክምና ያለው በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል እንደሆነ በነገሯቸው መሰረት በፍጥነት ወደዚያው ቢወስዱትም፤ እዚያም በደም ግፊት ወይም በስትሮክ ክፉኛ የተመታው እዮብ በውጪ አገር የተሻለ ህክምና እንደሚያስፈልገው በተነገራቸው መሰረት ለህክምና ከተጠየቀው 25ሺህ ዶላር ውስጥ ቅድሚያ 22 ሺህ ዶላር ተከፍሎ በቅርብ ውደሚገኘው ወደናይሮቢ ጆሞ ኬንያታ ሆስፒታል ወስደውታል።
ይሁንና ለቀናት ራሱን የሳተው የ37 ዓመቱ አርቲስት እዮብ ፤ናይሮቢ ሆስፒታል በገባ በማግስቱ እስከወዲያኛው አሸልቧል።
የኢሳት ወኪል ባደረሰን መረጃ መሰረት የእዮብ አስከሬን ዛሬ ጧት 1፡00 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፤ የቀብር ስነ-ስርዓቱ ነገ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
ተወዳጁ አርቲስት እዮብ መኮንን የአንዲት የ13 ዓመት ሴት ልጅ አባት ነበር።
የኢሳት ባልደረቦች ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ፣ ለአድናቂዎቹና በእዮብ ሞት መሪር ሀዘን ለደረሰባቸው ሁሉ መጽናናት ይሆንላቸው ዘንድ ልባዊ ምኞታቸውን በድጋሚ ይገልጻሉ።