የቁጫ ሕዝብ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ጠየቀ።

ነሃሴ ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው የቁጫ ሕዝብ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ እንጠይቃለን” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ፓርቲያችን አንድነት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚታገልላቸውና ገዥው ፓርቲ ከወረቀት አልፎ ያልተገበራቸው ሀገራዊ ቁምነገሮች ውስጥ ዜጎች ሳይሸማቀቁ በነፃነት ሃሳባቸውንና አመለካከታቸውን የመግለፅ፣ በነጻነት የመደራጀት፣ በገዛ ሀገራቸው በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ በፈለጉበት አከባቢ የመኖር፣  የመደገፍ፣ የመቃወም እና  ስለመብታቸው ሳይሸማቀቁ የመጠየቅ  መብቶች እንደሚገኙበት  አመልክቷል።

እንዲሁም በአጠቃላይ የሕግ በላይነት መስፈን፣ የሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች መከበር፤ ከዚህም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ  እና የዜጎችን ዋስትና ማረጋገጥ፤ ፓርቲው ከሚታገልላቸው የዲሞክራሲ ምሰሶዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጿል።

የቁጫ ሕዝብም ያነሳቸው የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የአስተዳደር ጥያቄዎች ከዚህ ተነጥሎ እንደማይታይ የገለጸው አንድነት ፓርቲ፤  የአካባቢው ነዋሪዎች በሠላማዊ መንገድ፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ጥያቄያቸውን ለመንግሥት ቢያቀርቡም የተሰጣቸው ምላሽ እስርና ማስፈራሪያ መሆኑ ፓርቲያችንን አሳዝኖታል ብሏል።

ከግንቦት 28 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ ዞን በቁጫ ወረዳ የሆነው ነገር የዜጎችን ህጋዊ ጥያቄ በሕገ-ወጥነት መቀልበስ መሆኑን መካድ አይቻልም  ብሏል አንድነት።

በጅምላ የታሰሩትና አሁንም እስር ላይ የሚገኙት ህጋዊና ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን ያመለከተው አንድነት፤  ፓርቲያችን ጉዳዩን በቅርበት ተከታትሎ እንዳጣራው በርካቶች በጅምላ የታሰሩበት ምክንያት፦” ልጆቻችን አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ ይማሩ፣ በስማችን ልንጠራ ይገባናል፣ የማንነት ጥያቄያችን ምላሽ ያግኝ፣ ፍትህና መልካም አስተዳደር ይረጋገጥ፣ የልማት ጥያቄያችን ምላሽ ያግኝ የሚሉና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን የመብት ጥያቄዎች በማንሳታቸው  እንደሆነ ገልጿል፡፡

እነዚህን የዜጎች ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብቶች ስርዓቱ “አረጋግጫቸዋለሁ” በሚላቸውና በቁጥጥር ስር ባደረጋቸው ሚዲያዎቹ የሚለፍፋቸው ቢሆኑም፤ ለቁጫዎች የተሰጣቸው ምላሽ ግን ሰብዓዊ ክብራቸውን መጣስና ማሰር ነው ያለው አንድነት፤” ፓርቲያችን ይህንን ሕገ-ወጥ ተግባር አጥብቆ ይቃወማል፡፡”ብላል።

የፓርቲው መግለጫ  በመጨረሻም ፦”መንግስት የመብትና ማንነት ጥያቄ ስላነሱ ያሰራቸውን በአስቸኳይ እንዲፈታ፤ ቁጫዎች ያነሷቸውን ጥያቄዎች አግባብ ባለው መንገድ በፍጥነት እንዲመልስ እንጠይቃለን!!!” በማለት ጥሪ አቅርቧል።