(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 5/2011) የኢትዮጵያን የምርጫ ስርአት ለመገምገም ኢትዮጵያ የገቡት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልኡካን ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየት ጀመሩ።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት ያህል በኢትዮጵያ የሚገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቴክኒክ ቡድን አባላት በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግና በምርጫ ስርአቱ ላይ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመወያየት ላይ መሆናቸው ተመልቷል።
ከአንድ አመት ተኩል በኋላ ይካሄዳል በሚል አስቀድሞ መርሃ ግብር የተያዘለትን ምርጫ በተመለከተ እየተደረገ ያለው ውይይት በምርጫው ግዜ ሰሌዳ ላይ ስለሚኖረው እንድምታ የታወቀ ነገር የለም።
የተባበሩት መንግስታት ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ይካሄዱ የነበሩ ምርጫዎችንም በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ዩ ኤን ዲ ፒ በኩል ይደገፍ እንደነበርም ታውቋል።
ነጻ ምርጫ በሌለበትና መቶ በመቶ አንድ ፓርቲ አሸናፊ በተባለበት ሒደት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድጋፍ ሲሰጥ ቆይቷል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቢሮ ሃላፊ በኋላም የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ረዳት አስተዳዳሪ የነበሩት ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ ለምርጫው ድጋፍ እንዲደረግ አይነተኛ ሚና እንደነበራቸውም ሒደቱን በቅርብ የሚያውቁ ያስታውሳሉ።
በኢትዮጵያ በምርጫ ስም በሕዝብ ላይ ለሚፈጸም ጥፋት የተባበሩት መንግስታት ድጋፍ ማድረጉን የሚተችና እነዚህን ወገኖች ኢትዮጵያዊው የትልቁ ተቋም ሃላፊ ደግሞ ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው ታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ከእንግዲህ ለእውነተኛና ነጻ ምርጫ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል።