የተቃዋሚ መሪዎች ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው

ታኀሳስ ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የተከሰሱት 6 የተቃዋሚ ድርጅቶች አመራሮችና ሌሎች ዜጎች በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት ሁለት ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጠባቸው ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ የስድስት ተከሳሾችን ሁለት ጉዳዮች ለማየት ተሰይሞ የነበረ ሲሆን ቀደም ብሎ ተከሳሾች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየደረሰባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ ቀርቦ እንዲያስረዳ ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የሰጠውን ትዕዛዝ ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቃል ተሰምቶ በመቅረጸ ድምጽ ተቀድቶ እንደገና በጽሑፍ ተገልብጦ ከመልስ ጋር እንዲቀርብ ቢያዝም ፣ ድምጹ በወረቀት ተገልብጦ ስላልደረሰ ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ መልሱን ይዞ እንዲቀርብ መታዘዙን ጋዜጣው ዘግቧል።

ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ መቃወሚያ ላይ የቀረበውን የፌደራል አቃቤ ህግ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።