የተምች ወረርሺኝ በመላ ሃገሪቱ ቡቃያዎችን እያጠቃ ነው፡፡

ሰኔ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፀረ ሰብል ተባይ ወይም ተምች ወረርሽኝ በአማራ  በኦሮሚያ ዞን፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣በሰሜንና በደቡብ ወሎ፣  በትግራይ  ደቡባዊ ዞን በአላማጣና ራያ አዘቦ ወረዳዎች ቡቃያዎችን እያጠፋ ነው፡፡

በባህላዊ ዘዴዎችና በኬሚካል ርጭት ለመከላከል ሙከራ ቢደረግም  ለውጥ አለመምጣቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

የተምች ተባይ ወረርሽኝ በአማራ  በምስራቅ ጎጃም በ11 ወረዳዎች ውስጥ በ12 ሺ 849 ሄ/ር የሰብል ማሣ ላይና በ2 ሺ 670 ሄ/ር የግጦሽ መሬት ላይ ቢከሰትም እስካሁን የተወሰደ በቂ እርምጃ የለም። ዞኑ የኬሚካል እጥረት እዳለበት አሳውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜንና በደቡብ ወሎ የተምች ወረርሺኝን  በቁጥጥር ስር ለማዋል አስቀድሞ ባልተደረገ ዝግጅት ምክንያት በርካታ አርሶ አደሮችን አስደንግጦዋል፡፡

አላማጣና ራያ አዘቦ ወረዳዎች ውስጥ የተከሰተውን የተምች ወረርሺኝ  በባህላዊ ዘዴዎችና በኬሚካል ርጭት ለመከላከል እየተሞከረ  ሲሆን በደቡብ  በኮቸሬ ወረዳ በ18 ሄ/ር ላይ በቦሎቄና ጎመን ላይ ትል ተከስቶ በባህላዊ የመከላከል ዘዴ በቁጥጥር ስር ለማዋልም ጥረት እየተደረገ ነው።

በደቡብ  በኮንሶ ልዩ ወረዳ የግሪሳ ወፍ ፣ በቤንሻንጉል – ጉሙዝ ደግሞ የአይጥ መንጋ ሰብሎችን እያወደሙ እንደሚገኝ ከተለያዩ ክልሎች ግብርና ቢሮዎች የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።