የተለያዩ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች የጋራ የትግል ሸንጎ መሰረቱ

ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የተለያዩ የፖለቲካ እና ሲቪክ ማህበራትን በማካተት ከግንቦት10 እስከ 13 በካናዳዋ ዋና ከተማ ኦታዋ በተደረገው ጉባኤ ፣ በአሁኑ ወቅት በስልጣን ላይ የሚገኘውን የህወሀት/ ኢህአዴግን መንግስት ለመታገልና የኢትዮጵያን ህዝብ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ላለፉት 2 አመታት በተደረገው ጥረት ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ” የተባለ ህብረት መመመስረቱን ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

ህብረቱን ከፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ህብረት፣ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ዲሞክራት፣ ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር፣ ትንሳኤ ኢትዮጵያ አርበኞች ህብረት፣ ታጠቅ እርበኞች ግንባር፣ የኢትዮጵያ መድህን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሁም ከ7 ያላነሱ የሲቪክ ተቋማት በጋራ የመሰረቱት ነው።

ጉባኤው ከሸንጎው ጋር አብረው ለመታገል የሚፈልጉ ደርጅቶች ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነትና ሉአላዊነት እንዲሁም በሀገሪቱ የግዛት አንድነት ላይ ግልጽና የማያወላውል እምነት መያዝ፣ የማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ዲሞክራሲያዊ ሰብአዊ መብቶቹን ማክበር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነት እንዲኖር መታገል፣ እንዲሁም የህወሀትን መንግስትና ስርአት የአፈናና ጭቆና ስርአት መለወጥና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር መተካት እንዳለበት ማመን የሚሉ መርሆዎችን አስቀምጧል።

ጉባኤው ዶ/ር ኤርምያስ ዓለሙን በሊቀመንበርነት፣ ፕ/ር አቻምየለህ ደበላን በምክትል ሊ/መንበርነት፣ አቶ ግደይ ዘራጺዮንን በጸሀፊነት እና አስራደው ከበደን በፋይናንስ ሀላፊነት መርጧል።

በመጨረሻም ጉባኤው ሸንጎው ያወጣቸውንና የጸደቀቻቻውን አምስት መርሆዎች የሚቀበሉ የሲቪክ ድርጅቶችና ግለሰቦች የህብረቱ አባል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

የጉባኤው ሂደት በጥሩ መንፈስ የተካሄደ እንደነበር ምክትል ሊቀመንበሩ ፕ/ር አቻምየለህ ደበላ ለኢሳት ገልጠዋል።

በጉባኤያችሁ ማጠቃለያ ላይ ሸንጎውን ሊቀላቀሉ የሚፈልጉ ድርጅቶች የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉአላዊነት የሚቀበሉ መሆን አለባቸው በማለት ያወጣችሁት መርሆ፣ የብሄር ድርጅቶች ወደ እናንተ እንዳይመጡ አስቀድሞ የሚከለክል አይሆንም ወይ ለተባለው ጥያቄ ፣ ችግር እንደሌለውና ሸንጎው ከድርጅቶች ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጠዋል።

ጉባኤውን የመሰረቱት ድርጅቶች በመገናኛ ብዙሀን እና በህብረተሰቡ ውስጥ በስፋት አይታወቁም፣ ታዋቂዎችን የብሄርና የህብረብሄር ድርጅቶች ለማካተት መኩራ ተደርጎ እንደሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰሩ ጥረት መደረጉን፣ ጥረቱም እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide