በደቡብ አፍሪካ ለአቶ መለስ ዜናዊ የተያዘው መርሀ ግብር እንዲሰረዝ ተደረገ

ግንቦት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበር አባላት ባደረጉት ተጽእኖ ለአቶ መለስ ዜናዊ የተያዘው መርሀ ግብር እንዲሰረዝ ተደረገ

አቶ መለስ ፣ ታቦ ምቤኪ አፍሪካን ሌደርሽፕ ኢንስቲቲዩት የተባለ ተቋም  ፣ በሚያዘጋጀው  ጉባኤ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች እና ምሁራን በሚገኙበት ዛሬ ሜይ 24፣ 2012 ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ ተገልጾ ነበር።

ዝግጅቱን በተመለከተ ተቋሙ የሚከተለውን ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር ” የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒሰትር በአመታዊው የታቦ ምቤኪ የአፍሪካ ቀን አመታዊ ትምህርት ሜይ 24 ፣ 2012 በ18 ሰአት በዜኬ ማቲውስ ታላቅ የመሰብሰቢአ አዳራሽ ፣ በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ንግግር ያደርጋሉ። የአቶ መለስ ትምህርት “አፍሪካ በአዲሱ የአለም ስርአት፡ ፈተናዎችና እና እድሎች” በሚልላይ ያተኩራል። ከትምህርታቸው በሁዋላ ለእርሳቸውና ለታቦ ምቤኪ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል።

ማስታወቂያው ስለ አቶ መለስ ዜናዊ የህይወት ታሪክም ያብራራል። ይሁን እንጅ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ትናንት ያደረጉት ተቃውሞ፣ በተቋሙ ውስጥ በስራ አስፈጻሚነት ከሚሳተፉት መካከል ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ ባደረጉት ከፍተኛ ተቃውሞ፣ ተቋሙ ለአቶ መለስ ይዞት የነበረውን መረሀ ግብር ለመሰረዝ መቻሉን ለማወቅ ተችሎአል።

የድርጅቱ አስተባባሪ የሆኑት ላኪ ፎሳ ዝግጅቱ መሰረዙን ለኢሳት አረጋግጠዋል ። ምክንያቱን እንዲናገሩ የተጠየቁት ፎሳ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ይሁን እንጅ ከስራ አስፈጻሚዎች መካከል አንዱ የሆኑት ፕ/ር ማሞ ሙጨ ለአቶ መለስ ተይዞ የነበረው መርሀ ግብር የተሰረዘበት ምክንያት ኢትዮጵያውያን በአሰሙት ተቃውሞ ነው ብለዋል።

ፕ/ር ማሞ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በነበሩት ዝግጅቶች ላይ የአፍሪካ መሪዎች ተጋብዘው ንግግሮችን አድርገዋል። እርሳቸው የኮሚቴ አባል ሆነው አቶ መለስ ሲጋበዙ ማየት ሳይዋጥላቸው ቀርቶ እንደነበር ፕ/ር ማሞ ተናግረዋል።

አቶ መለስ በቅርቡ በቡድን 20 አገራት ስበሰባ ላይ በጋዜጠኛ አበበ ገላውና በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞአቸው እንደተመለሱ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide