ግንቦት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከ14 የግል ኮሌጆች የተሰባሰቡ ከ5 ሺ በላይ የሚጠጉ የህክማን ተማሪዎች ሰኔ 27፣ 2005 ዓም የጀመሩትን የትምህርት ማቆም አድማ የቀጠሉ ሲሆን መንግስት ለችግራቸው መፍትሄ የማይሰጥ ከሆነ በአድማው ለመግፋት መወሰናቸውን ተናግረዋል።
የትምህርት ሚ/ር ባለስልጣናት ተማሪዎቹ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ፣ የተማሪዎች ተወካይም እስከትናንት ድረስ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሲነጋገር ከቆየ በሁዋላ ተማሪዎች ሊያገኙት አለመቻሉን መዘገባችን ይታወሳል።
የተማሪዎች ተወካይ የሆነው ተማሪ እያሱ ኩሚሳ ትናንት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት ውጤት ለማስገኘት ባለመቻሉ ተማሪዎች በትምህርት ማቆም አድማው ለመግፋት መወሰናቸውን ዛሬ ከኢሳት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ገልጿል።
የትምህርት ሚኒስቴር ባለስልጣናት ችግሩን መንግስት እንደፈጠረው ቢያምኑም ለማስተካካል እንደማይችሉ ግን ገልጸውልናል አለው ተማሪ እያሱ፣ ተማሪዎቹ የፈለገው ቢመጣ አንማርም የሚል አቋም ሲይዙ፣ ባለስልጣናቱ” አንድን ግንብ ስታዩት የማይወድቅ መስሎ ከታያችሁ አትጋፈጡትም፣ ነገር ግን ሳስቶ የምታዩት ከሆነ ግን እንጥለዋለን ብላችሁ ለመግፋት ትሞክራላችሁ፤ የእናንተ ጉዳይም እንደዚሁ ነው አርፋችሁ ብትቀመጡ ይሻላችሁዋል ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጿል።
መንግስት የክሊናካል ነርስ ተማሪዎችን በተመለከተ በድንገት ያወጣው አዲስ መመሪያ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ ተማሪዎች እንደተቃወሙት መግለጻችን ይታወሳል። በጉዳዩ ዙሪያ ዛሬም የመንግስት ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።