ሰማያዊ ፓርቲ መንግስት ለቀረቡት ጥያቄዎች በ3 ወራት ውስጥ መልስ እንዲሰጥ አሳሳበ

ግንቦት ፳፱ (ሀያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ግንቦት29 ቀን 2005 ዓም ባወጣው መግለጫ መንግስት በፓርቲው ላይ መሰረተቢስ ውንጀላ ከማቅረብ ይልቅ ለቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጥ ጠይቋል።

የገዥው ፓርቲ ተወካይ ሰልፉን አስመልክቶ “የሐይማኖት አክራሪነት አጀንዳው አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ድብቅ አጀንዳው ገሃድ ወጣ” በማለት የሰጡት አስተያየት መሰረተ ቢስ ፍረጃ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው ፣ የገዥው ቡድን አባላት ለንግግራቸውና ለሚሰጡት አስተያየት ሚዛን የሌላቸው ከመሆኑ ውጭ በፓርቲው ፕሮግራምም ሆነ እንቅስቃሴ ከአሸባሪነት ጋር የሚያገናኘውን አንዳችም ነገር አልጠቀሱም ብሎአል፡፡

ፓርቲው “በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ እና በሕገ መንግስቱ በተሰጠው መብት ተጠቅሞ በሕጋዊ ሥነስርዓት ያደራጀውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በእንዲህ አይነት መንገድ መፈረጅ ሰልፉ ከተጠራበት ዓላማና መንፈስ በእጅጉ የራቀ አስተያየት ሆኖ አግኝተነዋል” ብሎአል።

የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገዥው ፓርቲ በበጎ ጎን አለማየቱንና የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ሁሉ ወደ ሽብርተኝነት ፍረጃ ለመክተት የሚያደርገውን ጥረት የሚያመላክት ሆኖ ማግኘቱን የገለጠው ሰማያዊ ፓርቲ፣  ገዥው ፓርቲ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንደሆኑ አድርጎ እንደማያያቸውም ለመገንዘብ መቻሉንም ገልጿል።

የእስልምና እምነት ተከታይ ዜጎቻችን ማንኛውንም የመብት ጥያቄ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር በሰላማዊ መንገድ የማቅረብ ሕገ መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን መንግስትም ሆነ ገዥው ፓርቲ እንዲያውቀው እናሳስባለን ያለው ፓርቲው ፤ ሰማያዊ ፓርቲ ከመንግስትም ሆነ ከገዥው ፓርቲ በሚሰጥ ማንኛውም ማስፈራሪያ ከጀመረው የሰላማዊ ትግል ጉዞ ፍፁም ወደ ኋላ እንደማይል፤ ይልቁንም የተነሱትን የሕዝብ ጥያቄዎች መንግስት በሦስት ወራት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስቧል።