(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት1/2011ፕሬዝዳንት ሳህለወረቅ ዘውዴን ጨምሮ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እና ክልላዊ መንግስታት እንዲሁም የዓለም ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በኢትዮጵያ ዓየር መንገድ የአውሮፕላን አደጋ በጠፋው የሰው ህይወት ማዘናቸውን ገለጹ’።
የአውሮፕላን አደጋው መድረሱን ተከትሎም በርከታ የዓለም ሀገራት ህዝቦች፣ የሀገራት መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ይገኛሉ።
ፕሬዝዳንት ሳህለወረቅ ዘውዴና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የፌዴራል መስሪያ ቤቶች እና ክልላዊ መንግስታት በአውሮፕላኑ አደጋ ለሞቱት ሰዎች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዩ ጉቴሬዝም በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ በናይሮቢ የሚካሄደው የተመድ የአካባቢ ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ ሲጓዙ የነበሩ የስራ ባልደረቦቻቸው እንደተነበሩ አረጋግጠዋል።
የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዩ ጉቴሬስ በአውሮፕላን አደጋው የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ፥ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም፥ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን ሲገልጹ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
በአደጋው በርካታ ዜጎቿን ያጣቸው ካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ተሩዶም በትዊተር ገፃቸው ላይ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ካናዳውያን እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።
የፈረንሳይ መንግስትም በአውሮፕላን አደጋው የስምንት ዜጎቹ ህይወት ማለፉን በመግለጽ በአደጋው ዙሪያ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአውሮፕላን አደጋው ህይወታቸውን ላጡ ዜጎቻቸው እና የሌሎች ሀገራት ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይም፥ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ሰባት የብሪታኒያ ዜጎችና በተጨማሪ ለሌሎች ሀገራት ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።
የጀርመን መራሄተ መንግስት አንግላ መርክል፥ በአውሮፓላን አደጋው ለጠፋው የሰው ህይወት ማዘናቸውን በቃል አቀባያቸው ማርቲና ፊዬትዝ በኩል አስታውቀዋል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም በአውሮፕላን አደጋው ሀይወታቸውን ካጡት ውስጥ የሶማሊያ ዜጎች እንደሚገኙበት በማስታወቅ፥ የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሞሃሙዱ ቦሃሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአውሮፕላን አደጋው ዜጎቻቸውን ላጡ ሀገራት በሙሉ የሀዘን መግለጫ ልከዋል።