በኦሮሚያ በማንኛውም ብሔር ላይ የማፈናቀል ሙከራ አልተደረገም

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት3/2011) በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በማንኛውም ብሔር ላይ የማፈናቀል ሙከራም ይሁን ሌላ ጉዳት አልደረሰም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገላጻ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ እንደገለጹት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም በቄለም ወለጋ ዞን በሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም።

ቢሮ ሃላፊው ይሕንን መግለጫ ለመስጠት የተገደዱት “በቄለም ወለጋ ዞን የሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ጫና እየተደረገባቸው ነው” የሚል ዜና በኢሳት መለቀቁን ተከትሎ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በማንኛውም ብሄር ላይ የማፈናቀል ሙከራም ይሁን ሌላ ጉዳት አልደረሰም ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ገልጿል።

በቄለም ወለጋ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ግን አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ በሚሉ ሃይሎች እየተሰቃዩ መሆናቸውን ለኢሳት አስታውቀው ነበር።

የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ ችግሩ የሕይወት መስዋዕትነት የሚያስከፍል መሆኑንም በመገለጽ።

በአካባቢው ያለው መከላከያም ሆነ የጸጥታ ሃይሉ እንዲሁም  የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ ምንም አይነት ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ነበር የገለጹት።

በቄለም ወለጋ ዛሬ ላይ ችግር የገጠማቸው ዜጎች በ1977ቱ የሰፈራ ፕሮግራም ከወሎ ተነስተው በቄለም ወለጋ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የአማራ ክልል ተወላጆች ናቸው። እነዚህ ተወላጆች ደግሞ ቁጥራቸው በሺ የሚቆጠር መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

ቄሮን አስከትሏል የተባለውና ታጠቀ የተባለው ቡድን አካባቢው የእነሱ አለመሆኑና ወደ መጡበት መመለስ እንዳለባቸው መመሪያ አስተላልፏል ይላሉ ለኢሳት በሰጡት መረጃ ።

ኢሳት በአካባቢው የተፈናቀሉና አካባቢውን ልቀቁ የተባሉ ሰዎችን አነጋግሮ መረጃውን ቢለቀም እንዲህ አይነቱ ዜና ሆነ ተብሎ በኦሮሚያ ክልል ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር የማይፈልጉ አካላት ያቀዱት ነው ብለዋል የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ  አቶ አድማሱ።

ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማደፍረስ የሚደረጉ ተግባራት በሙሉ በህግ የሚያስጠይቁ መሆኑንም ሀላፊው አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ወንድሞቹ ከሆኑት የኢትዮጵያ ብሄሮና ብሄረሰቦች ጋር አንድ ላይ በመሆን ሀገር እንደገነባ አሁንም ቢሆን ሀገር የመገንባት ስራውን ቀጥሏል ብለዋል።

ቢሮ ሃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ በኦነግና በኦዴፓ ካድሬዎች ጫና በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከኦሮሚያ እየተፈናቀሉ መቆየታቸው ይታወቃል።